ግቦቹን ለማሳካት በሴቶች፣ በወጣቶችና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ መሥራት እንደሚገባ ተመለከተ

ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በሴቶች፣ በወጣቶችና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ መሥራት እንደሚያስፈልግ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ኃላፊ ገለጹ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት /ተመድ/ ቀን በኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ የድርጅቱን ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል ትናንት ተከብሯል።

ኃላፊው ዶክተር ካርሎስ ሎፔዝ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ድርጅቱ እኤአ 2030 ለማሳካት ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት የወጣቶችን ሥራ አጥነት መቀነስ፣ ሴቶችን ማብቃትና ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር በትኩረት ሊሰራባቸው ይገባል።

የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የደቡብ ሱዳንና የሳህልና አካባቢው አገሮች አለመረጋጋትና የተፈጥሮ አደጋዎች ግቦቹን በማስፈጸም ረገድ ተግዳሮቶች ሊሆኑ ቢችሉም፤ ፈተናዎቹን አልፎ ለውጤት ለመብቃት መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአባል አገሮች ቁርጠኝነት በድርጅቱ ለተነደፉት 17 የልማት ግቦች ስኬታማነት ወሳኝነት እንዳለውም ገልጸዋል።

ዓለም ጤናማና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት እንድትሆን ሰብዓዊ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ዶክተር ሎፔዝ አሳስበዋል።

አገሮች የአየር ንብረት ለውጡን ለመቋቋምና የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ሊከተሉ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ሚስ አሁና ኢዚአኮንዋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት የያዘችው አቋም የዘላቂ ልማት ግቦችን ወደ ተግባር ለመተርጎም ያስችላታል ብለዋል።

ድርጅቱ በኢትዮጵያ ''ተልዕኮውን በስኬት እያከናወነ ነው'' ያሉት ተወካይዋ፣የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን በመደገፍ እንደሚሰሩ ገልጸዋል

ተመድ የተመሰረተው እኤእ 1945 ሲሆን፣ቀኑ መከበር የተጀመረው ከምስረታው ከሦስት ዓመታት በኋላ ነው።(ኢዜአ)