ክላሲ የታሸገ ውሃ በህብረተሰቡ ጤንነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ

በላይ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚያመርተው ክላሲ የታሸገ ውሃ በህብረተሰቡ ጤንነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ መረጋገጡን  ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በንግድ ሚኒስቴር የገበያና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት እንደተናገሩት ድርጅቱ ከ2007-2009 ዓ.ም በተደረገ የጥራት ፍተሻ በተደጋጋሚ የጥራት ጉድለት የታየበት በመሆኑ እንዲታገድና ምርቱ ከገበያ ላይ እንዲሰበሰብ ተደርጓል፡፡

የምርት ጥራቱን እንዲያስተካክል የውዴታ ግዴታ እንዲፈርም በመደረጉ ማስተካከሉ ተረጋግጦ ታህሳስ/2009 ዓ.ም እገዳው ተነስቶለት ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉ ተገልጿል ፡፡

ሚያዚያ/2010 ዓ.ም በተደረገ የገበያ ኢንስፔክሽን ሥራ የምርቱ ናሙና ተወስዶ በተደረገው የላብራቶሪ ፍተሻ ውሃው በድጋሚ የጥራት ደረጃውን ያላሟላ ሆኖ ተገኝቷል ያሉት አቶ ካሳሁን ክላሲክ የታሸገ የመጠጥ ውሃ በህብረተሰቡ ጤንነት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ ስለተረጋገጠ ህብረተሰቡ ውሃውን እንዳይጠቀም አሳስበዋል፡፡ (ምንጭ:የንግድ ሚኒስቴር)