ዋልታ ቴሌቭዠን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድርን በቀጥታ ለማስተላለፍ ከአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር ተስማማ

ዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት  እና የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ  ውድድርን በቀጥታ የቴሌቭዠን ሥርጭት ለማስተላለፍ ትላንት የሁለትዮሽ ስምምነት ፈጽመዋል ።

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 11 ፤ 2011 ዓ.ም ድረስ ስምንት ቡድኖችን በማሳተፍ በአዲስ አበባ ስታድየም ይከናወናል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ መከላከያ፣ ጅማ አባጅፋር፣ አዳማ ከተማ፣ ወላይታ ድቻና የናይጄሪያው ኳራ ዩናይትድ መሳተፋቸውን ሲያረጋግጡ ስምንተኛ ቡድን በቅርቡ ይታወቃል፡፡

ሁለቱ ተቋማት ጨዋታውን በቀጥታ ለማስተላለፍ ሲስማሙ ውድድሩን ለመከታተል የማይመቻቸው የስፖርት ቤተሰብ  ባለበት ቦታ ሆነው ጨዋታዎችን እንዲከታተል በማሰብ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ኃይለየሱስ ፍስሃ እንዳሉት ጨዋታዎችን በቀጥታ ለማስተላለፍ የተፈለገበት ሌላው ምክንያት የውድድሩን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦች እንደሚያገኙት ደረጃ ከስታድየም ከሚገኘው ገቢ በመቶኛ ተሰልቶ የሚከፈላቸው መሆኑም  በፊርማ  ሥነ ሥርዓቱ  ላይ ተገልጿል፡፡