11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ነገ በሐዋሳ ከተማ ይጀምራል

11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ነገ በሐዋሳ ከተማ እንደሚጀመር ተገለጸ።  

አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ባካሄዷቸው ጉባኤዎች የፓርቲዎቻቸውን ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን፤ የፓርቲያቸውን ሊቀ-መንበርና ምክትል ሊቀመንበር በመምረጥ 11ኛውን የኢህአዴግ ጉባኤ ለመካፈል በዛሬው ዕለት ወደ ሐዋሳ ጉዞ ጀምረዋል።

ሐዋሳ ላይ በሚደረገው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ለመሳተፍ ተወካዮቻቸውን እያሳወቁ ነው፡፡ 

 ባለፉት ቀናት አራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች ባካሄዷቸው ድርጅታዊ ጉባኤዎች የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የዓርማ እና መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ አድርገዋል፡፡

በተመሳሳይ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) እና የሕዝዊ ወያኔ ኃርነት (ሕወኃት) የስያሜና ዓርማ ለውጥ ሳያደርጉ በሐዋሳ ጉባኤ ይሳተፋሉ ፡፡

ሁሉም የግንባሩ አባል ፓርቲዎች እና ድርጅቶች የማዕከላዊ ኮሚቴዎቻቸውን በአመዛኙ በአዳዲስ አመራሮች ተክተው የሚገናኙ  በመሆኑ  ጉባኤውን ልዩ ያደርገዋል ።

11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የሚጠበቁ ጉዳዮች
1. በነሐሴ ወር 2007 በመቀሌ ከተማ ተደርጎ በነበረው 10ኛ የኢህአዴግ ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችን መሠረት በማድረግ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሠሩ ሥራዎች ሪፖርት ቀርበው ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በጥልቀት ከገመገመ በኋላ ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያሳይ እና ለ12ተኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የሚሆን ሰነድ እንደሚያዘጋጅ ይጠበቃል፡፡
2. ሁሉም የግንባሩ አባል ፓርቲዎችና ድርጅቶች በቅርቡ ባካሄዷቸው ጉባኤዎች የመረጧቸውን አዳዲስ የማዕከላዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሎቻቸውን በዚህ ጉባኤ በማሳተፍ አዲስ የኢህአዴግ ምክር ቤት ይመሠርታሉ፡፡
3. ወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ በጥልቀት ይገመገማል፤ ለውጡን ለማስቀጠል አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ፤ የቀጣይ አቅጣጫዎች ይመላከታሉ፡፡
4. ባለፈው መጋቢት ወር ጥልቅ ተሐድሶውን ተከትሎ የተቀመጡ አቅጣጫዎች እና በተደረገውን የአመራር ለውጥ የተሠሩ ተግባራት ይገመገማሉ፡፡
5. አዲስ የኢህአዴግ ምክር ቤት መመሥረቱን ተከትሎ የድርጅቱን ሊቀ-መንበርና ምክትል ሊቀ-መንበር ይመረጣል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎች

ከአራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች የተወከሉ ከእያንዳንዳቸው 250 በአጠቃላይ 1000 ተሳታፊዎች  በቀጥታ በምርጫውና በውሳኔዎች ዙርያ በድምጽ የሚሳተፉ ይሆናሉ፡፡
 

በልዩ ሁኔታ 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ተሳታፊዎች 

በታዛቢነት የሚገኙ ግን ድምጽ የማይሰጡ ተሳታፊዎች፡-

ሴቶችና ወጣቶች
አጋር ድርጅቶች
የተለያዮ የህብረተሰብ ክፍሎች
ማኅበራት
ፌዴሬሽኖች
ዩኒቨርሲቲዎች
የፌዴራል ተቋማት ኃላፊዎች
ልማታዊ ባለሀብቶች  ናቸው ።

11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ መክፈቻ ላይ የሚሳተፉ
• የሠራዊት አመራሮች
• አርቲስቶች
• ስፖርተኞች
• ታዋቂ ግለሰቦች
• ተፎካከሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
በጥቅሉ አንድ ሺህ 900 ተሳታፊዎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡