የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ሠራተኞች በተቋሙና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄዱ

የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የአሁንና ቀድሞ ተማሪዎች እንዲሁም የዩኒቨርስቲው ሠራተኞች በተቋማቸውና ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂደዋል፡፡

በአዲስ አበባ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ግቢ በተካሄደው  መድረክ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲና የአካባቢውን ማህበረሰብን  ለመደገፍ ያለመ ነው ።

በዩኒቨርስተው ተምረው የተመረቁ፣ በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ እና በተቋሙ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ የተማሪ ተወካዮች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች በውይይት  መድረኩ ተገኝተዋል፡፡

ውይይቱ ዩኒቨርስቲውንና በአጠቃላይም የሀገር ዕድገትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጥናቶችን ለማካሄድ፣ የበጎ ፈቃድ ማህበራትን ለማጠናከር እንዲሁም በዪኒቨርስቲና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መስራት ባለባቸው ሁኔታዎች መወያየታቸውንም ዶክተር ዳምጠው ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ የተገኙት ተሳታፊዎቹ በጨረታ እና በሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች ለዩኒቨርሲቲው የበጎ አድራጎት ክለብ እና ለማህበረሰቡ የሚሆን 8መቶ ሺህ ብር ለማስረከብ ቃል ገብተዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው ስድስት ካምፓሶች ያሉት ሲሆን በየዓመቱ ከ200 በላይ የሆኑ የምርምር ስራዎችን እንደሚሠራም ለማወቅ ተችሏል፡፡