በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን የሚያጡት ወጣቶች በመሆናቸው በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን የሚያጡ እና ለአካል መጉደል ሰለባ የሚሆኑት ወጣቶች እንደመሆናቸው መጠን በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ በአመት በትራፊክ አደጋ ምክኒያት 1.3 ሚሊየን ሰዎች ህወታቸውን ያጣሉ፡፡

በኢትዮጵያም ከ2005 እስከ 2010 ድረስ በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር በ30 በመቶ መጨመሩን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ይህንን ምክንያት በማድረግም በየዓመቱ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ህዳር ወር በገባ በሶስተኛው ሳምንት እሁድ የመንገድ ትራፊክ ተጎጂዎች ማስታወሻ ቀን ተብሎ እንዲከበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በወሰነው መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ 15 ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡

ዘንድሮም ‘መንገዶችም ታሪክ አላቸው’ በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ አቤት ሆስፒታል እና ፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን አላማውም ሀብረተሰብ ላይ ግንዛቤን በመፍጠር በትራፊክ አደጋ ለህልፈት እና ለአካል ጉዳት የሚዳረጉትን ቁጥር ለመቀነስ እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡

ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆንም የትራፊክ አደጋ ክትትል እና ቁጥጥር ላይ በስፋት ለመስራት ያለመ እንደሆነ ነው አዘጋጆቹ የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን የሚያጡ እና ለከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚዳረጉት ወጣቶች እንደመሆናቸው መጠን የሃገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ከተለያዩ ባለድርሻ ድርጅቶች የተሳተፉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ 

በትራፊክ አደጋ ምክንያት እየደረሰ ያለውን አደጋን ለመከላከል እና  ለመቀነስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተባብረው መስራት እንደሚገባቸው የገለጹት ተሳታፊዎች በቴክኖሎጅ በመታገዝ የሚሰራው ስራም ተጠናክሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም አሽከርካሪዎች እና እግረኞች ህግ ሊያከብሩ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡