ከህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ በ19 መዝገቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

ከህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ወንጀል ጋር በተያያዘ በ19 መዝገቦች ላይ ክስ መመስረቱን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡

በዚህም በ15 መዝገቦች ላይ የተከሰሱ 14 ተከሳሾች የዋስትና መብታቸው ተከልክሎ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ ነው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል  አራት ተከሳሾች በአራት መዝገቦች ላይ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው በመከታተል ላይ እንደሚገኙ በአቃቤ ህግ  የኢኮኖሚ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፉአድ ኪያር ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በኮንትሮባንድ ንግድ ሲዘዋወሩ 60  ሺህ 94 የተለያዩ ሽጉጦች፣ 161 ሺህ 695 የተለያዩ የሽጉጥ ጥይቶች፣ ዘጠኝ ከባድ መትረየስ፣ አምስት ክላሾች፣ ሁለት ዝናር የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች በጉሙርክ ህግ መሰረት ለመንግስት ገቢ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡

አሁን ስራ ላይ ባለው አዋጅ ላይ ክፍተት በመኖሩ  አዋጁን ለማሻሻል እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ (ምንጭ፡-ጠቅላይ አቃቢ ህግ)