78ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል ተከበረ

78ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል ዛሬ በመላ አገሪቱ በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተክብሮ ዋለ፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዓሉ በተከበረበት በአዲስ አበባ አራት ኪሎ የድል ሀውልት ተገኝተው ለኢትዮጵያ ህዝብ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ ባስተላለፉት መልዕክታቸው የድል በዓል የኢትዮጵያዊያንን አይበገሬነት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓሉ የፋሽስቶችን የቂም እና የበቀል እርምጃ ያፈረሰ፣ የኢትዮጵያዊያንን ጽናት፣ አይበገሬነትና አንድነት ዳግም ያረጋገጠ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ክስተት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የሉዓላዊነትን፣ ክብር እና የሀገርን ዋጋ በአግባቡ የምንረዳ ህዝቦች ነን ያሉት ፕሬዝደንቷ በድሉ ላይ የታየውን የአርበኞችን አንድነት ተምሳሌት በማድረግ የጋራ ክንዳችንን በድህነት ላይ በማሳረፍ ድል በማድረግ ከታሪክ ተወቃሽነት መውጣት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ፕሬዝደንቷ አያይዘውም “ከሚያለያየን በላይ የሚያዋህደን ነገር በርካታ ነውና አንድ ላይ ሆነን ለሁላችንም የምትሆን ሀገር ከመገንባት የተሻለ አማራጭ እንደሌለ አንርሳ፤ ተባብረን ወደ ማማው እንውጣ፤ የኢትዮጵያን ዳግም ውልደትም እናውጅ፤” ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው የድል በዓል በሁሉም አቅጣጫ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለወራሪው የጣሊያን ጦር አውቅና ሳይሰጡ ድል ያደረጉት ቀን መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 የአርበኞች ታላቅ ገድል ዘላለማዊ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ እና አርበኞችንም መርሳት እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

ጣሊያን የአድዋን ድል ለመበቀል በሚል በጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቤኒቶ ሙሶሎኒ አማካኝነት፥ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን መውረሯ የሚታወስ ነው።

በወቅቱ የነበሩት ኢትዮጵያውያንም ወራሪውን ሀይል ለአምስት ዓመታት በጽናት ታግለው 1933 ዓ.ም ድል ነስተውታል።

የወቅቱ አርበኞች ለሀገራቸው ነጻነት የከፈሉትን መስዋዕትነት እና ያስገኙትን ድል ለማሰብም፤ በየአመቱ ሚያዚያ 27 ተከብሮ ይውላል።

በበዓሉ ላይም ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ አርበኞች እና በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።