የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒት የፈጠረው መላመድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

ተላላፊ በሽታዎችን ለማከም አገልግሎት ላይ የሚውለው የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒት ለበሽታዎች የፈጠረው መላመድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዳይሬክቶሬት ዳይሬተር ወይዘሮ አስናቀች አለሙ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተላላፊ በሽታዎችን ለማከም አገልግሎት ላይ የሚውለው የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒት ለበሽታዎች የፈጠረው መላመድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በህክምና ባለሙያ የታዘዙ መድኃኒቶች በአግባቡ ያለመጠቀም፣ መድኃኒትን ለራስ የማዘዝ ባህል እየተስፋፋ መምጣት፣ ያለ ሃኪም ማዘዣ መድኃኒቶችን ከፋርማሲዎች መግዛት እና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ የኮንትሮባንድ መድኃኒቶችን መጠቀም መድኃኒቱ እንዲላመድ አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው ዳይሬክተሯ የተናገሩት፡፡

ችግሩን ለመፍታት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እየተሰጡ ስለመሆናቸውና ያለ ማዘዣ የሚሸጡ ፋርማሲዎች ላይ የቁጥጥር ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም መድኃኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ናሙና በመውሰድ የፍተሻ ስራ እንደሚከናወን ታውቋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሽብርተኝነትና ከአየር ንብረት መዛባት በመቀጠል የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒት መላመድ በደህንነት ስጋት ውስጥ ተካቷል፡፡ ስጋቱ በኢትዮጵያም እንደሚስተዋል ነው የተገለጸው፡፡