በማይናማር ፓይለቱ አውሮፕላኑን ያለፊት ጎማ በማሳረፍ 89 ሰዎችን ከአደጋ ታደጋቸው

በማይናማር የፊት ጎማ የመዘርጋት እክል የገጠመው አውሮፕላን በአብራሪው ጥረት አሳፍሯቸው የነበሩ 89 ሰዎችን አደጋ ሳያጋጥማቸው ማሳረፍ መቻሉ ተሰምቷል።

ንብረትነቱ የማይናማር ብሔራዊ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላን ማንዳላይ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ነው ሊያርፍ የቻለው።

አብራሪው ማንዳላይ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰ በኋላ ለሁለት ጊዜያት ያህል መዞሩ ተነግሯል።

ሆኖም የፊት ጎማው አልታዘዝም ማለቱን የአየር መንገዱ ባለስልጣናት ጠቅሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ አብራሪው የአደጋ ጊዜ መፍትሔ ከሆኑት ውስጥ ክብደቱን ለመቀነስ ነዳጁን እንዳቃጠለ ባለስልጣናቱ አብራርተዋል።

በመጨረሻም አብራሪው የአውሮፕላኑ አፍንጫ መሬት ከማስንካቱ በፊት የኃላ ጎማውን ማኮብኮቢያው ላይ ማሳረፍ ችሏል።

በዚህም አውሮፕላኑ ለ25 ሰከንዶች ያህል ማኮብኮቢያው ላይ ከተንሸራተተ በኋላ 89ኙም ተሳፋሪዎች ያለምንም ጉዳት ሊተርፉ መቻላቸው ተነግሯል።

ከአደጋው በኋላም የማይናማር የትራንስፖርት ሚኒስቴር የፓይላቱ ስራ እጅግ የሚደነቅ እንደነበር ለሮይተርስ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ባለፈው ሳምንት አጋማሽም 17 ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ አደጋ የተከሰተ ሲሆን፥ የአሁኑ አጋጣሚ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ተብሏል።/ቢቢሲ/