የእውቀት መጨረሻ ግቡ ማህበረሰብን መጥቀም እንጂ መጉዳት አይደለም – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

የእውቀት የመጨረሻ ግብ ለማህበረሰብ መጥቀም እንጂ መጉዳት አይደለም፤ እናውቃለን የሚሉ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ከእነዚህ ታዳጊዎች መማር አለባቸው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዘጠነኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ነው፡፡

ግንቦት 29 ቀን የተጀመረው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሳምንት በዛሬው ዕለት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተጠናቋል፡፡

ኢኖቬት ኢትዮጵያ በሚል ስያሜ በአራት አበይት ኹነቶች የተከበረው ይህ ሳምንት፤ የአይሲቲ አውደ ርዕይ፣ ኢትዮያን እናንሳት (ስታርት አፕ ኢትዮያ)፣ ቴክኖሎጂን እናዘምን በሚል ሃሳቦች የተካሄደ ሲሆን በኮንፈረንሱ የፈጠራና የምርምር ስራዎች የእውቅናና ሽልማት ስነ-ስርዓቶች ተካሂዷል፡፡

በዘንድሮው ዘጠነኛው የሽልማት ስነስርዓት ላይ ከመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተወጣጡ 177 ተማሪዎች፣ ሰልጣኞች፣ መምህራንና አሰልጣኞች በፈጠራ ስራዎቻቸው ተወዳድረው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በሽልማቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መፍጠር በአዕምሮ የተሳለን በተግባር ማስቀመጥ መሆኑን ገልጸው፣ የፈጠራ ባለቤቶች በተግባር ያስቀመጡትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በየፈጠራ ዘርፉ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እና ባለሀብቶች የፈጠራ ባለቤቶችን መደገፍ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የፈጠራ ስራ ፈጠራ እንዲሆን የፈጠራ ስራዎች በየጊዜው መሻሻል እና መተቸት እንደሚገባቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእውቀታቸው ለኢትዮጵያ ከፍለው የሰጡ እንዳሉ ሁሉ በእውቀታቸው ጨለማን፣ መለያየት እና መጠፋፋትን የሚዘሩ መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው እነዚህን ታዳጊዎች እና የፈጠራ ባለቤቶች ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ የምርምር እና የፈጠራ ስራቸው ተግባራዊ እንዲሆን እንጥራለን ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም ሌሎች የፈጠራ እና የምርምር ሰራዎችን ለማፍራት ትምህርት ቤቶች እና ወላጆቻቸው በትኩረትና በቅርበት መስራት አለባቸውም ነው ያሉት፡፡