ኢቦላ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው

በኬኒያ እንደተከሰተ እየተነገረ ያለው ኢቦላ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት አስታወቀ፡፡

የኢኒስቲቲዩቱ ም/ ዳይሬክተር ዶ/ር በየነ ሞገስ በኬኒያ ኬሪቾ ካውንቲ አካባቢ አንድ ሰው በኢቦላ ቫይረስ መጠቃቱ ተጠርጥሮ ውጤቱ ግን ኔጌቲቭ መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሆነም ነው ዶ/ር በየነ የጠቆሙት፡፡

በተጨማሪም በሃገሪቱ በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 614 መድረሱን ኢኒስቲቲዩቱ በመግለጫው አስታወቋል፡፡

ከነዚህም ውስጥ 294ቱ በኦሮሚያ ክልል ሲሆን የሁለቱ ህይወት ማለፉን ም/ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ደግሞ በ70 ሰዎች ላይ የኮሌራ ምልክት የታየባቸው ሲሆን የህክምና ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ መደበኛ ህይወት ተመልሰዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በትግራይ ክልል 18 ሰዎች በበሽታው የተጠቁ ሲሆን በድረዳዋ ደግሞ አንድ ሰው በበሽታው መያዙ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

እንደ ኢንስቲቲዩቱ መግለጫ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ክልሎች 18 የለይቶ ማከሚያ ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

በክልሎቹ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን የመለየት ስራ መሰራቱንም መግለጫው አውስቷል፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከልም ከ17 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች በ2 ዙር ክትባት ለመስጠት የታቀደ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ክትባት ነገ ሰኔ 12/2011 መስጠት እንደሚጀመርም ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ የኮሌራ ወረርሽኝ በአፍሪካ በዘጠኝ ሃገራት የተከሰተ መሆኑንም ዶ/ር በየነ አስረድተዋል፡፡

በሽታውን ለመቆጣጠር እንዲቻል ለሁሉም ክልሎች መድሃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች መሰራጨታቸውም ተጠቁሟል፡፡

የኮሌራ ህክምና እና ክትባት አቅርቦት በአለም አቀፍ ደረጃ አነስተኛ በመሆኑ ክትባቱና ህክምናው የሚሰጠው በጣም ተጠቂ እና ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በሌላም በኩል የቺኮግኒያ ወረርሽኝ በሶማሌ ክልል በቀብሪ ደሃር ከተማ በ115 ሰዎች ላይ መከሰቱም ተገልጿል፡፡

ወረርሽኙ በአካባቢው በሚገኘው የመከላከያ ካምፕም የተከሰተ ሲሆን በ25 ሰዎች ላይ ተስተውሏል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን ስድስት ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ መከሰቱን ዶ/ር በየነ ገልጸዋል፡፡ በባህርዳር ዙሪያ ወረዳዎችም እንዲሁ የወባ ወረርሽኝ መከሰቱ ተገልጿል፡፡

የኩፍኝ በሽታም በአፋር ክልል መከሰቱን መግለጫው የጠቆመ ሲሆን በክልሉ በአሁኑ ወቅትም 26 ህሙማን በህክምና ተቋማት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው፡፡

በተያያዘም የጊኒ ወርም በሽታ በጋምቤላ ክልል ጎግ ወረዳ በአራት ዝንጀሮዎች ላይ በመገኘቱ ወደ ሰዎች እንዳይተላለፍ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ከክረምቱ ጋር ተያይዞ በተለይም በጎርፍ ምክንያት ውሃዎች መበከል ሊያጋጥማቸው ስለሚችል ህብረተሰቡ ውሃን አክሞ ወይም አፍልቶ መጠጣት እንዳለበት ተገልጿል፡፡