በአዲስ አበባ ፍቃድ ካላቸው ኤምባሲዎችና ፖስታ ቤቶች ውጭ የሞተር ብስክሌት እንዳይንቀሳቀስ ተከለከለ

በአዲስ አበባ ከተማ ከሰኔ 30 ጀምሮ ፍቃድ ካላቸው ኤምባሲዎችና ፖስታ ቤቶች ውጭ ምንም አይነት ሞተር ብስክሌት በከተማዋ እንዳይንቀሳቀስ መወሰኑን ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ አስታውቀዋል።

በከተማዋ በሞተር ሳይክል የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ከፀጥታ አካላት ጋር ለአንድ ሳምንት ጥናት መካሄዱን ተከትሎ ውሳኔው የተላለፈ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባ እየተፈጠረ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ለማቅለል እና የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት በከተማዋ ከጧቱ 12:00 እስከ ምሽቱ 1:00 በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ምንም ዓይነት የከባድ መኪና ተሽከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ ተወስኗል።

በከባድ መኪኖቹም ሆነ በሞተር ሳይክሎቹ ላይ የተደረገው ክልከላ ባለንብረቶቹ ሁኔታዎችን እስከሚያመቻቹ እስከ ሰኔ 30 ተግባራዊ አይደረግም ነው የተባለው፡፡

በሌላ በኩል የከተማውን የፀጥታ ተቋማት እንደ አዲስ በማዋቀር በአሰራርና በሎጂስትክ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በአስተዳደሩ አዳዲስ ወጣቶችን በማሰልጠን ወደ ፀጥታ ስራ ለማሰማራት የምልመላ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችን ለማከናወን በርካታ ቅድመ ዝግጅቶች መከናወኑን በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

የአቅም ደካሞችን ቤት የማደስ፣ ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች ወደ 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ደብተሮችን ለመሰብሰብ፣ የደም ልገሳ ፕሮግራም ለማከናወን፣ ችግኞችን ለመትከልና በሌሎች በርካታ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን ለማከናወን መታቀዱን አክለው ገልጸዋል፡፡

ሕብርተሰቡ በከተማዋ የመልካም አስተዳድር ሥራዎች፣ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት እና በጸጥታ ሥራዎች ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡