አስፈጻሚ አካሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር ላይ መላላት ይስተዋልበታል ተባለ

በህግ የበላይነት ዙሪያ በተደረገው ጥናት የህግ አስፈጻሚ አካሉ መላላት እንደሚስተዋልበት ተለይተዋል ተባለ፡፡

ምንም እንኳን በኢትዮጲያ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ለውጦች ቢመዘገቡም የህግ የበላይነት አለመስፈን በሀገሪቱ ጎልቶ የሚስተዋል ድርጊት ነው፡፡

የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ መቼም ቢሆን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው የሚሉት የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎው ሽፕ ኢትዮጲያ ፕሬዝዳንት  ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ በዚህ ረገድ መንግስት በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ይላሉ፡፡

በህግ የበላይነት ዙሪያ በተለይ ከከተማ ውጭ ግጭቶች የተነሱባቸው ቦታዎች ላይ ጥናት አድርገናል የሚሉት አቶ ዳንኤል የጥናቱ ግኝቶች የህግ አስፈጻሚ አካሉ ላይ መላላት እንደሚስተዋል እና የተደራጁ ቡድኖች የፍትህ ስረአት ላይ ጣልቃ በመግባት ፍትህ እንዳይሰፍን ማድረጋቸውን ያሳያልም ነው የሚሉት፡፡

በኢትዮጲያ የህግ የበላይነት ይሰፍን ዘንድም የመንግስት መጠንከር፤የጸጥታ ሀይሉ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ መስራት እና ህዝቡ ለሰላም የሚሰጠው ትኩረት በጥናቱ የተቀመጡ የመፍተሄ አቅጣጫዎች ስለመሆናቸውም ነው የተጠቆመው፡፡