ጅቡቲ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ ወደብ ገነባች

ጅቡቲ  ዘርፈ ብዙ  አገልገሎት የሚሠጥ ዘመናዊ ወደብ  መገንባቷን አስታወቀች ።

ጅቡቲ የገነባችው አዲሱ  ወደብ  የዶራህሌ ወደብ  የመሰረተ ልማት ዘርፍ አቅሟን ያሚያሳደግ  ነው ተብሏል፡፡

የምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ጅቡቲ በአፍሪካ እጅግ ዘመናዊ የተባለ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ ወደብ ገንብታለች ፡፡

ዶራሌህ የሚል ስያሜ የተሠጠው ወደብ ግንባታው እኤአ በ2015 የተጀመረ ሲሆን በ690 ሄክታ መሬት  ላይ ነው ያረፈው ነው፡፡

የወደቡ መገንባት ጅቡቲ በዘርፉ ዓለም ዓቀፍ  ተደራሽነትን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የምታደርገውን ጥረት የሚያጠናክር ነው ተብሏል፡፡

የወደቡ ግንባታ በአጠቃላይ 590 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን ወጭው በጅቡቲ መንግስት፣በቻይናና በጅቡቲ ነፃ ቀጣና ባለስልጣን መሸፈኑን ማሪን ኢንሳይት ድረ ገፅ አስነብቧል፡፡ የግንባታ ሥራውም በቻይና ኩባንያ ነው የተከናወነው፡፡

የወደብ ልማቱ ለጅቡቲ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዋናው ሞተር መሆኑን የጅቡቲ ወደቦች እና ነጻ ቀጠና ባለስልጣን ሊቀመንበር አቡቦከር ኦማር ሃዲ ተናግረዋል።

አሁን የተገነባው ወደብም ይህንኑ የሚጠናክር እንደሆነ ነው ጨምረው የገለፁት፡፡ ለዓለም በወደብ ዘርፍ ዘመናዊ መሠረተ ልማትን በመገንባት አቅማችንን ማሳየት በመቻላችንም ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡

ወደቡ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ከተዘረጋው 752 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ፕሮጀክት ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡

የሁለቱን አገራት የቆየና ታሪካዊ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከርም ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተወስቷል፡፡

እስያ ፣ አፍሪካና አውሮፓን በማስተሳሰር የዓለም የንግድ መስመር ማዕከል ለመሆን የበቃችው ጅቡቲ በዶራሌህ ወደብ ደረጃዋን ከፍ ማድረግ ችላለች ተብሏል፡፡

ከአገሪቱ መዲና ጅቡቲ በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው አዲሱ ወደብ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚመጡ 30 ሺ መርከቦች በየዓመቱ ያቋርጡታል፡፡ ወደቡ ከእስያ ሀገራት 59 በመቶ፣ ከአውሮፓ 21 በመቶ ከአፍሪካ ደግሞ 16 በመቶ የንግድ እቃዎችን ያስተናግዳል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 95 በመቶ የሚሆነውን የወጭና የገቢ ንግድ ዕቃዎችን የምታስተናግደው የጅቡቲ ወደብን በመጠቀም ነው፡፡

23ሺ ስኬር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያላት ጅቡቲ 900ሺ ያህል የህዝብ ብዛት እንዳላት ከዓለም ባንክ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡