ደቡብ ሱዳን ኃይል እና መሠረተ ልማት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ልታስተናግድ ነው

ደቡብ ሱዳን በኃይልና በመሠረተ ልማት ላይ ትኩረቱን ያደረገ የምክክር መድረክ ልታስተናግድ  ነው ።

የምክክር መድረኩ ጁባ በመሰረተ ልማት ነዳጅ እና ዘይት ምርቷ ላይ ዘላቂ አሰራር እንድትተገብር የሚያስችላት ነውም ተብሏል፡፡

በ2011 ከሱዳን ነፃነቷን አግኝታ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ መንግስትን የመሰረተችው አገር በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተባለውን ጉባኤ ልታስተናግድ እንደሆነ ሱዳን ትሪቡን እያስነበበ ይገኛል፡፡

አገሪቱ በመጪው ጥቅምት ወር ላይ ታካሂዳለች የተባለው በኃይል እና መሠረተ ልማት ላይ ትኩረቱን ያደረገው ጉባኤ ለጁባ የልማት ጉዞ እንቅስቃሴ እና በአገሪቱ ፖለቲካ ላይም አዎንታዊ ተጽእኖይኖረዋል እየተባለ ይገኛል፡፡

ከአፍሪካ ቀንድ አገራት በከርሰ ምድር ነዳጅና ዘይት የበለፀገች እንደሆነች የሚነገርላት ደቡብ ሱዳን፤ ባለፉት ዓመታት በገጠማት የእርስ በእርስ ጦርነት ሳቢያ ተፈጥሮዋ ኢኮኖሚዋን ሳይጠቅም እንደቆየ ይነገራል፡፡

የአሁኑ ጉባኤም በዚሁ ጉዳይ ላይ መፍትሔን የሚያስቀምጥ ነው፡፡ አለማቀፍ የተፈጥሮ ማዕድን  አበልፃጊ ኩባንያዎች እና አገራት ጋር በጥምረት ለመስራት የምትችልበት አቅጣጫ ይዘረጋል ተብሏል፡፡

አፍሪካን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረትም አገሪቱ ከጎረቤቿ እኩል እንድትሆንም የፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር መንግስት የሚያቀርበው ምክረ ሀሳብ ላይ ይመከርበታል፡፡

ጉባኤው በአፍሪካ ህብረት የነዳጅ እና ኃይል ጉዳዮች ኮሚሽን የተዘጋጀ ሲሆን አህጉራዊ ይዘት ያለው ነው፡፡

የጥቅምቱን ጉባኤ ርዕሰ መዲናዋ ጁባ ታስተናግዳለች፡፡ ፕሬዝደንት ኪርን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት ተወካዮች የኢንዱስትሪ ተመራማሪዎች፣ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እና ባለሃብቶች ይታደሙበታልም እየተባለ ይገኛል፡፡

የአፍሪካ አገራት የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም በተመለከተ በደህንነት፣ ቴክኖሎጂ እና የመሰረተ ልማት ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ቀርበው አገራቱ እንደሚመካከሩባቸው እና ወጥ አቅጣጫም እንደሚይዙ ይጠበቃል ሲል የዘገበው ሱዳን ትሪቡን ነው፡፡