ቻይና በአፍሪካን ቁጥር አንድ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ በሞሮኮ ልትገነባ ነው

ቻይና በአፍሪካ ቁጥር አንድ የሆነ ሰማይ ጠቀስ  ህንጻ  በሞሮኮ ልትገነባ መሆኑን  አስታወቀች ።

እኤአ በ2017 መጀመሪያ ይፋ በሆነው መረጃ መሰረት በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የሚገኘው  የካርልተን ሴንተር የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ በመባል መሰየሙ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ቻይና በሞሮኮ መዲና ራባት ለመገንባት የተስማማችው ህንጻ በርዝማኔው ከካርልተን ህንጻም ይልቃል ነው የተባለው፡፡

የግንባታው ስምምነት በቻይናው የባቡር መንገድ ስራ ኮንስትራክሽንና በሞሮኮው ቢ ኤም ሲ ኢ ባንክ ኦፍ አፍሪካ መካከል በካዛብላንካ የተከናወነ ሲሆን ለግንባታው ከ375 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር  በላይ ወጪ ይደረግበታልም ተብሏል፡፡

55 ፎቅ ያለው  ይህ ህንጻ 250 ሜትሮችን  የሚረዝም ሲሆን በዲዛይኑ ዝግጅት ወቅት ስነ-ምህዳራዊ ጉዳዮች ትኩረት ያገኛሉም ተብሏል፡፡

እንደ ሌ 360 ማ ኒውስ ዘገባ ከሆነ ህንጻው በውስጡ የተለያዩ ቢሮዎች፣ ሆቴሎችና የተቀናጡ አፓርታማዎችን ያካትታል፡፡

የዚህ ህንጻ ግንባታ ሞሮኮ ቦሬግሬግ ሸለቆን ለማልማት የያዘችው ትልቅ ፕሮጀክት የመጀመርያው ምዕራፍ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በተጨማሪም የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች የሚከናወኑበት ቤተ-ሙከራ፣ የራባት ትልቁ ቴአትር ቤት፣ የሞሮኮ የባህል እና ስነ-ምድር ሙዚየሞችን በውስጡ ያካትታልም ተብሏል፡፡

ከአፍሪካ ሃገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ በሰማይ ጠቀስ ህንጻዎቿ የምትታወቅ ሲሆን በአህጉሪቱ ከሚገኙ እና በርዝመታቸው ቀዳሚ ከሆኑ 10 ህንጻዎች ውስጥ 5ቱ በደቡብ አፍሪካ ነው የሚገኙት፡፡ ( ምንጭ: ዠንዋ)