ኡጋንዳና ታንዛኒያ የድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ስምምነት አደረጉ

ኡጋንዳና ታንዛኒያ የድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ 

ኡጋንዳና  ታንዛኒያ  3 ነጥብ 55 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚጠይቀውን  የድፍድፍ  ነዳጅ  ማስተላለፊያ  ቧንቧ  መስመር ዝርጋታ ለማስጀመር  የሁለቱ ሃገር መሪዎች የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡

ኡጋንዳ የምታመርተውን ድፍድፍ ነዳጅ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በማሰብ ነው ይህ የቧንቧ መስመር የሚዘረጋው፡፡

የመስመሩ ግንባታ በይፋ መጀመሩን የሚያበስረው የመሠረት ድንጋይ በታንዛኒያው መሪ ጆን ማጉፉሊ እና በኡጋንዳ አቻቸው ዩዌሪ ሙሴቪኒ በወደብ ከተማዋ ታንጋ ተቀምጧል፡፡

የመስመሩ ዝርጋታ ከ3ነጥብ 55 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግበት ሲሆን የኡጋንዳን ድፍድፍ ነዳጅ ከምዕራባዊ ሆይማ ዲስትሪክት ወደ ታንዛኒያዋ የወደብ ከተማ ታንጋ የሚያስተላልፍም ይሆናል፡፡ 

በአጠቃላይ 1 ሺህ 445 ኪሎ ሜትሮችን የሚረዝመው የዚህ መሥመር ስራን ለማፋጠን ግንባታው ከተለያዩ ቦታዎች እንደሚጀመርም ተመልክቷል፡፡

የፕሮጀክቱ ሪፖርት እንደሚያሳየው ነዳጅ አስተላላፊው ቧንቧ 24 ኢንች ዲያሜትር ሲኖረው በቀን እስከ 216 ሺህ በርሜል ነዳጅ ያስተላልፋል፡፡

የእያንዳንዱ ቤርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋም 12ነጥብ 2 የአሜሪካ ዶላር እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

የቧንቧ መስመሩ እሳትን መቋቋም እንዲችል ሆኖ የተሰራ ሲሆን በ1ነጥብ 2 ሜትር ጥልቀት ወደ መሬት ዉስጥ ይቀበራልም ነው የተባለው፡፡

ከነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ ዝርጋታ በተጓዳኝ የግንባታ መሳሪያዎች ማከማቻ ግንባታ፣ የተለያዩ ተክሎች ልማትና  ለስራው አጋዥ የሆኑ ተግባራት እንደሚከናወኑም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

የድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታው ስራ በፈረንጆቹ 2020 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡( ምንጭ:ዘሞኒተር)