ብራዚል ለታንዛኒያ ያበደረችውን 203 ሚሊዮን ዶላር መሰረዟን አስታወቀች

ብራዚል ለታንዛኒያ ያበደረችውን 203 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መሰረዟን አስታውቃለች፡፡

የብድሩ መሰረዝ በሁለቱም ሃገራት መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ያጠናክራል ተብሏል፡፡

ከብሪክስ አባል ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ብራዚል በ2016 ዓመታዊ ገቢዋ 1 ነጥብ 8 ትሪሊየን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፥ በዓለም  ግዙፍ የተባለ የምጣኔ ሃብት እድገት ካላቸው ሀገራት መካከል በሰባተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

 አሁን ደግሞ ከታንዛኒያ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ስትል የ203 ሚሊየን ዶላር የብድር እዳ መሰረዟን ገልፃለች፡፡

ታንዛኒያ እ.አ.አ በ1979 ከሞሮጎሮ እስከ ዶዳማ ያለውን መንገድ ለመገንባት  ከደቡብ አሜሪካ የኢኮኖሚ ሃይል 203 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድር ወስዳ ነበር፡፡

የብራዚል  የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ጊልሜ ሌዝ በብራዚል እና ታንዛኒያ መካከል የንግድ እና ፋይናንስ ግንኙነቶች በብድሩ ምክንያት መዘጋታቸውን ጠቁመዉ፥  በሁለቱ ሃገራት መካከል የተሻለ የንግድ ግንኙነት  ለመፍጠር ታንዛኒያ የነበረባትን ብድር ልንሰርዝ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በብራዚል የታንዛኒያ አምባሳደር ኢማኑዌል ናቺምቢ እና የብራዚል ብሄራዊ ግምጃ ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን ዶክተር ሶኒያ ፖርቴላ ብድሩን ለመሰረዝ በተስማሙ ጊዜ የብራዚል ኩባንያዎች በታንዛኒያ በተለያዩ  የኢንቨስትመንት ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከታንዛኒያ መንግስት ጋር በመወያያት ተስማምተዋል ።

አምባሳደር ናቺምቢ ብራዚል ታንዛኒያ ያለባትን ብድር መሰረዟን በማመስገን፥ የሃገሪቱ መንግስት ጠንካራ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት የሚሰራውን ጥረት እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ታንዛኒያ ከደቡብ አሜሪካ የኢኮኖሚ ኃይል ጋር ያላትን የንግድ እና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር በትኩረት እንደምትሠራም አምባሳደሩ አክለው ገልፀዋል፡፡

በታንዛኒያ የብራዚል አምባሳደር ካርሎስ አልፎንሶ በበኩላቸው ብድሩ መሰረዙ እንደ የብራዚል ልማት ባንክ ያሉ ዋና ዋና የብራዚል የፋይናንስ ተቋማት  የንግድ ብድርና የፋይናንስ ዕድሎች እንደሚከፍትላቸው ገልፀዋል፡፡

ይህ እንቅስቃሴ በአገራቱ መካከል ያለውን ጥሩ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የብራዚል ተቋማትን በተለያዩ የልማት ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶች ላይ በማስተዋወቅ የታንዛኒያ ኢኮኖሚ እንዲስፋፋ ያደርጋልም ብለዋል ።