ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ሃብቷን የሚያስተዋውቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ አካሄደች

ደቡብ ሱዳን ያላትን የነዳጅ ሀብት ለዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ማሳወቅን ያለመ ነው ያለችውን ዓለም ዓቀፍ ጉባዔ አካሂዳለች፡፡

በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪ የሆነው የዓለም አቀፍ ጉባኤው ከአፍሪካ የነዳጅና የኃይል አቅርቦት ህብረት ጋር በጋራ በመተባበር ነው የተዘጋጀው፡፡

የደቡብ ሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ጀምስ ዋኒኢጋ በመክፈቻ ዝግጅቱ ላይ እንደተናሩት በተለይም ባለፉት 18 ወራት የነበረው አለመረጋጋት ለነዳጅ ምርት አዳጋች ነበር፡፡

‹‹ አሁን ጊዜው የደቡብ ሱዳን ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሰል ዝግጅቶችን በማካሄድ ጁባ ያላትን ሀብትና አቅም ለዓለም ታሳያለች ብለዋል፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ነዳጅ በማምረት ለዓለም ገበያ እንደምታቀርብ ነው የተናገሩት፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም አመቱ ሀገሪቱ በኃይል አቅረቦት ያላትን እምቅ ኃይል በማሳደግ እድገቱዋን የምታፋጥንበት ነው፡፡

የሀገሪቱ ነዳጅ ሚኒስትር እዝቄል ጋትኮዝ በበኩላቸው ጉባዔው የነዳጅ ዘርፍን ሊያግዙ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማግኘትና መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት የጎላ ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡

አንዳንድ ባለሃበቶች ተገቢ ባልሆነ መንገድ በነዳጅ ዘርፍ በመሠማራትና ሃብቱን አላግባብ በመጠቀም ገቢያቸውን ለማሳደግ እንደሚሯሯጡ ለማወቅ መቻሉን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ በኩል የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር ለማስቆም ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ሲሉም ተሰምቷል፡፡

የህግ ባለሞያው ኤንጂ አዩክ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት አቅማቸውን በመገንባት የልማት ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው አሳስበው ደቡብ ሱዳንም በአህጉሪቱ የለውጥ ጉዙ ንቁ ተሳታፊ  የምትሆንበት ጊዜ ላይ ነች ብለዋል፡፡