ዙምባብዌ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ወደ አገሯ እንዳይገባ እገዳ ጣለች

ዙምባብዌ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ወደ አገሯ እንዳይገባ  እገዳ መጣሏን  አስታወቀች ።    

ዙምባብዌ  የበቆሎ ምርት ወደ ሃገሯ እንዳይገባ በሰኔ ወር ላይ እገዳ ጥላ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ  ወደ ሀገሪቱ በምታስገባቸው  የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ሌላ እገዳ ጥላለች ፡፡

ዙምባብዌ ባላፈው ዓመት ከሰማንያ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ወደ ሀገር ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን አስገብታለች፡፡

እነዚህ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ድንች፤ ካሮት፤ ማንጎ፤ ብርቱካን እና ሌሎችን እንደሚያጠቃልል ነው የሀገሪቱ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ  ያመላከተው፡፡

የሀገሪቱ የግብርና ሚኒስትር ጆሴፍ ሜድ  ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ መሆናቸውን ገልፀው ሀገሪቱ አሁን ባጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረትም  የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከውጭ የሚገቡ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እንዲቆሙ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን አስታውቀዋል፡፡

እገዳው የተጣለው የሀገሪቱ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬን መታደግ እንዲችሉ ነው ተብሏል፡፡

የሀገሪቱ የግብርና ሚኒስትር የእገዳው መጣል ዚምባብዌ የሀገር ውስጥ ምርቶቿን እንድታሳድግ አስተዋጾኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በተለይም የሀገሪቱ አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪውን እንዲታደጉ ያስችላቸዋልም ነው የተባለው፡፡ በተቃራኒውም ምርቶቿን የምታቀርበው ደቡብ አፍሪካ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖም ቀላል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

እገዳው በአስቸኳይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ሚኒስትሩ ገልጸው የሚመለከታቸው አካላትም ለገበያ የማይቅረቡ ከውጭ የሚገቡ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ዝርዝር በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡