ሶማሊያ በዛሬዉ ዕለት በከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ ሥር ሆና አዲስ ፕሬዝደንቷን መሐመድ ዓብዱላሂ ፎርማጆ መረጠች ።
ለምርጫ ከቀረቡት 20 እጩ ተፎካካሪዎች 4ቱ ወደ ቀጣዩ ምርጫ ተሻግረዉ በተካሄደዉ ሁለተኛ ዙር ምርጫ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበሩት የቀድሞዉ ጠቅላይ መሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ምርጫዉን አሸንፈዋል።
ስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት ሁሴን ሼኽ መሐመድ የመጀመሪያዉን ዙር በ89 ድምጽ እየመሩ የነበረ ሲሆን፤ መሐመድ አብዱላሂ በ72 ድምጽ ሲከተሉ ቆይተዋል።
ሁሴን ሼኽ መሐመድ ሽንፈታቸዉን መቀበላቸዉም ገልጸዋል።
የቀድሞዉ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሸሪፍ ሼኽ አሕመድ 49 ድምጽ ፤ የአሁኑ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦማር አብዲራሺድ አሊ ሻርማርኬ ደግሞ 37 ድምጽ አግኝተዋል።
ተንታኞች እንደገመቱት በመጀመሪያዉ ዙር ምርጫ የመራጩን ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ማንም ባለማግኘቱ ነበር ሁለተኛ ዙር ምርጫዉ የቀጠለዉ።
ዘገባዎች እንደሚያሳዩትም ሻርማርኬ «ወዴት እንደሚያመራ ያስታዉቃል» በማለት ከፉክክሩ ራሳቸዉን አግልለዋል።
አዲስ የተመረጡት የሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት በመቃዲሹ አዉሮፕላን ማረፊያ ነዉ ድምፃቸዉን ሲሰጡ የዋሉት።
ምርጫዉ የሚካሄድበት ስፍራ ከሌሎች ይበልጥ ደህንነትና ጸጥታዉ አስተማማኝ መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ። ያሁኑ ምርጫ ባለፈዉ ነሐሴ ሊካሄድ የታቀደ ነበር-(ዶችዌለ)።