በናይጀሪያ 11ሚሊየን ህዝብ የከፋ የምግብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ድርጅቱ አስጠነቀቀ

በናይጀሪያ 11 ሚሊየን ህዝብ እጅግ የከፋ የምግብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸዉ የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት አስጠነቀቀ ፡፡

ድርጅቱ የምርት ወቅት በሆነዉ ከሰኔ እስከ ነሐሴ ባሉት ጊዜያት በሰሜናዊ ናይጀሪያ የሚገኙ አካባቢዎች ለዚህ ችግር እንደሚጋለጡ ይጠበቃል ነው ያለው ።

በዚህ ክፉኛ ሊጠቁ እንደሚችሉ ከሚገመቱት ቦታዎችም ቦኮ ሃራም የተመሠረተባት ቦርኖ 65 በመቶ የሚሆነዉ ርሃብ የሚያሰጋዉ ዜጋ የሚገኝባት ግዛት ናት ።

ቦኮ ሃራም በፈጠረዉ ያለመረጋጋት ምክንያት 120 ሺ የሀገሪቱ ዜጎች አደገኛ ለሆነ የረሃብ አደጋ እንዲጋለጡ ማድረጉን ጨምሮ አመልክቷል ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች በበኩሉ እንደገለጸው ፤በዚህ ስፍራ ልጆች እየሞቱ ስለሆነ አፋጣኝ እርዳታ ካላገኙም በሚሊየን የሚገመቱት ይኸዉ ዕጣ ያሰጋቸዋል።

ሙስና እና በመንግሥት እና በእርዳታ ድርጅቶች መካከል ያለዉ ዉዝግብም ችግሩን እያወሳሰበዉ መሆኑም ተገልጿል።

ባለስልጣናት የአካባቢዉ መንግሥታት የእርዳታ እህሉን ይሰርቃሉ የሚለዉን ክስ እያጣሩ መሆኑን አሶሼየትድ ፕረስ ዘግቧል።

የናይጀሪያ መንግሥት ለእርሻ የሚያደርገዉን ድጋፍ ከፍ ማደርጉን ቢገልጽም፤ ሀገሪቷ የምግብ እጥረት ያለባት መሆኗን ነው የተመለከተው ።