የደቡብ ሱዳን  ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያየዩ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይታቸውም ላይ የሀገሪቱን ሰላም የማስከበር ሂደት በተመለከተ በትኩረት ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲግማር ጋብሬል ከደቡብ ሱዳን የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ውይይት ለማድረግ ዛሬ ከሰአት አካባቢ ጁባ ገብተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በጁባ አለም አቀፍ አየር መንገድ ሲደርሱ በደቡብ ሱዳን አቻቸው ዴንግ አሎር አቀባበል ተደርጎላቸውል፡፡

በዛሬው ውሏቸውም ፕሬዝዳንቱ ሳልቫኪርን ጨምሮ ከበርካታ የሀገሪቱ የመንግስት አካላት ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት በሀገራቱ ሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በሰላም እና በደቡብ ሱዳን ስላለው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ዙሪያ እንደተነጋገሩ አስታውቀዋል፡፡

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው በኡጋንዳ ለስራ በተጓዝኩበት ወቅት በርካታ ደቡብ ሱዳናውያኖችን መመልከት እንደቻሉ አስታውሰው ባልጠበቁት ሁኔታ በሀገራቸው ላይ ለወደፊት ሰላም ይፈጠራል ብለው እንደማያስቡ አብዛኛዎቹ ስደተኞች ሲያነሱ እንደሰሙም አስታውቀዋል፡፡

ሲግማር ጋብሬል በተጨማሪም እንደገለጹት አሁን ሀገሪቱ ያለውን ጦርነት ማንንም አሸናፊ የማያደርግ እና ውጤቱም የህዝብ እልቂት ብቻ በመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጦርነቱን በማቆም ወደ ሰላም ድርድሩ መግባት አለባቸው ብለዋል፡፡

ፕሬዚደንት ሳልቫኪርም በሰላም ዙሪያ ለመወያየት ያሳዩትን ቁርጠኝነት እንደሚያደንቁ እና ሀገሪቱ ላይ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ሌሎች ከፍተኛ የጀርመን ዲፕሎማቶችም የችግሩ መፍትሄ በራሳቸው እጅ እንደሚገኝ እና በጎረቤት ሀገራት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችም እንዲሳኩ ማገዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የጀርመኑ ሚኒስትርም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር በሰላም ዙሪያ መወያየት አለባቸው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ሚኒስትሩ የተለያዩ አለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ተቋማትን ወደ ሀገሪቱ በመግባት የነዋሪዎችን ሁኔታ ለማሻሻል የሚያከናውኑትን ተግባራት እንዲፈቅዱ እና እገዛ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡ ( ምንጭ:  ሲጂ ቲኤን)