በትግራይ 22 ነጥብ6 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፍቃድ አገኙ

በትግራይ ክልል 22 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ማግኘታቸውን የክልሉ ከተማ ልማት፣ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ ፡፡

በክልሉ የኢንቨስተሮች ፍሰት ከጊዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱን የቢሮው የኢንቨስትመንት ዋና ስራ ሂደት ውስጥ የኢንቨስትመንት ቡድን አስተባባሪ አቶ ለይኩን አብረሃ ለዋልታ ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ 22 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺ 853 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታልና ከ600 በላይ ባለሃብቶች በላይ ብልጫ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

የዚሁ ምክንያትም በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ፣በክልሉ እርሻ ኢንቨስተሮች መበራከት፣የሚሰጠው አገልግሎት ፈጣን መሆንና የህብረተሰቡ የኢንቨስትመንት ግንዛቤ እያደገ መምጣት መሆኑን አቶ ለይኩን አብራርተዋል ፡፡

ባለሃብቶቹ ፣በከባድ ኢንዱስትሪ ፣በእርሻ ፣በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣በሆቴሎችና ቱሪዝምንና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዳስትሪ መሰመራታቸውን ጠቁመዋል ፡፡

የልማት ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ ለ110 ሺ249 ስራ ፈለጋዎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አቶ ለይኩን ገልጸዋል፡፡