የድርጅቱ ወታደሮች ከጁባ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲለቁ የደቡብ ሱዳን መንግሥት አዘዘ

የደቡብ ሱዳን መንግስት የተባበሩት መንግስታት ወታደሮች የጁባ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡

የተባበሩት መንግስታት በበኩሉ ወታደሮቹ በስፍራው እንዲቆዩ የተደረገው ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን ነው ብሏል፡፡  

በጁባ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ የሠፈረውን የተባበሩት መንግስታት ጦር ነው ለቆ እንዲወጣ የደቡብ ሱዳን መንግስት የጠየቀው፡፡

የሃገሪቱ የመረጃ ሚኒስትር ሚካኤል ማኩዌ የተባበሩት መንግስታት ጦር ከሃገሪቱ ፈቃድና እውቅና ውጪ በአውሮፕላን ማረፊያው እንደሰፈሩ ጠቁመዋል፡፡    

ወታደሮቹ የታጠቁና በጦር ታንኮች የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው በአካባቢው ያለውን ውጥረት ይበልጥ እንዳባባሰውም ጠቁመዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ያሳሰበው የደቡብ ሱዳን መንግስት ለተባባሩት መንግስታት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቡድን መሪ ወታደሮቹን በአስቸኳይ ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ እንዲመልስ መጠየቁንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ 

ወታደሮቹ ወደ ካምፓቸው እንዲመለሱ ለቡድን መሪው ነገርናቸው እነሱም በጥያቄያችን መሠረት ወታደሮቻቸውን ከ ጁባ አውሮፕላን ማረፊያ አስወጥተውልናል ብለዋል፡፡

በጁባ የተባበሩት መንግስታት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቡድን መሪ የሆኑት ደቪድ ሺረር በበኩላቸው ቡድኑ የጁባ አውሮፕላን ጣቢያን የመቆጣጠር አላማ እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ ለሃገሪቱ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን ቁልፉ ስፍራ አውሮፕላን ጣቢያው በመሆኑ ወታደሮቹ በስፍራው እንዲቆዩ ተደርጓል  ብለዋል፡፡

ካለፈው የፈረንጆቹ አመት ሃምሌ ወር አንስቶ አራት ሺህ የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ኃይል በጁባ እንደሠፈረ ይታወቃል፡፡( ምንጭ: ከዘኢስት አፍሪካን)