የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ ለዘጠኝ ቀናት ተራዝሟል

የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ የሚካሄድበት ጊዜ በ9 ቀናት ተራዝሟል፡፡

ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ በሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ላይ በድጋሚ ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል።

የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበኩሉ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤቱ መሰረዝ ተጠያቂው የምርጫ ኮሚሽኑ ነው ብሏል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በተካሄደው ምርጫ ኡሁሩ ኬንያታ አብላጫ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ገልጾ እንደነበር ይታወቃል።

ይሁን እንጅ የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምርጫው ከተካሄደ ከጥቂት ቀናት በኋላ ተጭበርብሯል በሚል የቀረበለትን አቤቱታ በመቀበል የምርጫውን ውጤት ውድቅ በማድረግ በድጋሚ እንዲካሄድ ትእዛዝ አስተላልፏል።

ይህን ተከትሎ የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ምርጫውን በድጋሚ ለማካሄድ  የሚያስፈጽም ኮሚቴ አቋቁሞ እኤአ በጥቅምት 17 ለማካሄድ ቀጠሮ መያዙን አስታውቆ ነበር፡፡

ይሁን እንጅ ቀኑ ኮሚሽኑ የምርጫ ሂደቱ ማሻሻያዎች ስለሚያስፈልጉት ለዚህ ዝግጅት ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለቱ ምርጫው ለተጨማሪ 9 ቀናት ተራዝሟል።

በዚሁ መሰረት በድጋሚ የሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፈረንጆቹ ጥቅምት 26 ቀን የሚካሄድ ይሆናል።

ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝቡን ፍላጎት በመፃረር መፈንቅለ መንግሥት ፈጽሟል በማለት ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል።

ምንም እንኳ ህገመንግስታዊ ስርዓቱንና በድጋሚ ይካሄድ የተባለውን የምርጫ ሂደት ቢቀበሉትም በኬንያ በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ አራት ዳኞች የተከናወነዉ የመንግሥት ግልበጣ አይነት ነው ሲሉ ነው የተቹት፡፡ 

በሌላ በኩል የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን በድጋሚ ምርጫው ሁለቱ ዋነኛ ተፎካካሪዎች ብቻ እንደሚሳተፉም ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በምርጫው የማይሳተፉ ሌሎች ተፎካካሪዎች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንወስደዋለን ብለው ነበር።

በምርጫው በሰፊ ልዩነት የተሸነፉ ተፎካካሪዎች በድጋሚ ምርጫው ሌሎች ተፎካካሪዎችም ስላለን ልንካተት ይገባል ብለዋል።

ይሁን እንጅ በድጋሚ ምርጫው የወቅቱ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ ብቻ ይሳተፋሉ ነው ያለው ኮሚሽኑ።

ፕሬዝዳንት ኡሑሩ ኬንያታ እና የተቃዋሚዎቹ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ 

እኤአ በ2007 በተካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በተቀሰቀሰ ግጭት ከ1ሺ 200 በላይ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡

በኬንያ የምርጫ ሂደት ላይ አስተያየት እየሰጡ ያሉ የፖለቲካ ተንታኞች የኬንያ ፖለቲካል ሙቀት እየጨመረ ቢመጣም ሃገሪቱ በምርጫ ምክንያት ወደዳግም ግጭት ታመራለች የሚል ግምት የላቸውም፡፡