በፑንት ላንድ የፍተሻ ጣቢያ በደረሰው ጥቃት ሰባት ሰዎች ተገደሉ

አልሸባብ በሶማሊያ ፑንት ላንድ የፍተሻ ጣቢያ ላይ ባደረሰው ጥቃት ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ ከአስራ አንድ በላይ የሚሆኑት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ የሽብር ጥቃት ላይ ያነጣጠረው ጽንፈኛው አልሻባብ ቡድን ሰኞ እለት በሶማሊያ ፑንት ላንድ የፍተሻ ጣቢያ ላይ በምትገኝ ከፊል ራስ ገዝ ክልል ላይ  ባደረሰው ጥቃት  ሶስት ፖሊሶችን እና አራት ግለሰቦችን ገድሏል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ 

አሸባሪ ቡድኑ ከአንድ ወር በፊት በሶማሊያ ፑንት ላንድ ላይ ባደረሰው ጥቃት 12 ሰዎችን እንደገደለ ያስታወሰው ዘገባው አሁን ደግሞ  የአይን እማኞችን ጠቅሶ ያወጣው መረጃ አሸባሪ ቡድኑ አካባቢውን ለመቆጣጠር የፍተሻ ጣቢያው ፖሊሶች ጋር ባደረገው ውጊያ ከሞቱት ውጭ ቢያንስ አስራ ሶስቱ ላይ ጉዳት አድርሷል ነው የተባለው፡፡

ከማለዳው አንድ ሰዓት አካባቢ ታጣቂ የአልሸባብ ተዋጊዎች በሁሉም አቅጣጫ ሆነው ሲያጠቁን ነበር ያሉት የአካባቢው የፖሊስ አዛዥ አብዲ ፈታህ ሞሃመድ ባልደረቦቻችን ቶሎ ደርሰው አፃፋውን መልሰዋል ብለዋል፡፡

የፍተሻ ጣቢያውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረትም ሳይሳካላቸው ቀርቷል ነው ያሉት፡፡ የአልሸባቡ ወታደራዊ ዘመቻ ቃል አቀባይ አብዲያሲስ አቡ ሙሳብ በበኩላቸው ሰባት ወታደሮችን እንደገደሉ በመጥቀስ ጉዳት ያደረስንባቸው አስራ አንድ ወታደሮች ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ አልሸባብ ቦሳሶ የምትባለውን የፍተሻ ጣቢያ ተቆጣጥረው እንደነበር እና በኋላም ጥለው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ  ከአምስት ዓመታት በፊት  ሲያካሂደው በነበረ ጥቃት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪዎች ዝርዝር ላይ መስፈሩ ይታወሳል፡፡ ( ምንጭ: ሮይተርስ)