አሚሶም አልሻባብን መደምሰስ የሚያስችል አዲስ የተደራጀ ጥቃት እንደሚጀምር አስታወቀ

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል /አሚሶም/ አልሸባብን ከመሰረቱ ለመደምሰስ አዲስና የተደራጀ ጥቃት ለመሰንዘር ማቀዱን አስታወቀ፡፡

ለሶማሊያ ዕቅድ ስኬት የኢትዮጵያ ፤ የኡጋንዳና የጅቡቲ  መከላከያ ኃይሎች ድጋፋቸውን አሳይተዋል፡፡

ሶማልያ በአልሸባብ የሽብር ወጥመድ ውስጥ ከወደቀች ረጅም አመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሸባሪ ቡድኑም የተለያዩ ውስብስብ ስልቶችን በመጠቀም በሀገሪቱ ከፍተኛ የሽብር ጥቃቶችን በመሰንዘር የብዙዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ ሀገሪቱም ወዳልሆነ አቅጣጫ እንድታመራ ምክንያት ሆኗል፡፡

በቅርቡ እንኳን በከባድ ተሽከርካሪ ላይ በተጠመደ የቦንብ ፍንዳታ ምክንያት 358 ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በሀገሪቱ ያለውን ጦርነት እና አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስና የጥቃት ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ  ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰላም አስከባሪ ኃይል በሀገሪቱ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡

በሀገሪቱ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከተሰማሩ ኃይሎች መካከል የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል /አሚሶም/  ይገኝበታል፡፡ አሚሶም በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል /አሚሶም/አሸባሪውን አልሸባብ  ለመዋጋትና ከመሠረቱ ለመደምሰስ አዲስና የተደራጀ ጥቃት ለመሰንዘር ማቀዱን እያስታወቀ ይገኛል፡፡

ይህን አዲስና የተደራጀ ጥቃት በሶማሊያ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ባለው የሽብርተኛ ቡድን /አልሸባብ / ላይ ለመሰንዘርና ቡድኑን ከመሰረቱ ለመደምሰስ የሶማሊያ የመከላከያ ኃይልና የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በጥምረት  ለመሥራት ማቀዳቸውም ተገልጻል፡፡ 

የአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዳረጋገጡት  ይህን የተደራጀ ተልእኮ ለማካሄድና አሸባሪ ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሶማሊያ ምድር ለማጥፋት የሚያስችል ስራዎችን ለመስራት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህን ተልዕኮ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል /አሚሶም/ ከሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ጋር በመሆን በበላይነት ይመራዋል፡፡

እንደ አፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ገለጻ ከሆነ የተረጋጋች ሶማሊያን ለመፍጠርና አሸባሪውን አልሸባብን ከሀገሪቱ ለማጥፋት  የሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል /አሚሶም/ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ 

የተለያዩ ወታደራዊ ተንታኞች ግን  የሽብር  ቡድኑ  እየተጠቀመበት ያለውን ያልተለመደ ስልት ለመደምሰስ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ከሚገመተው በላይ የሰውና የንብረት ውድመት ሊያስከትል  እንደሚችል  ስጋታቸውን ከመግለጽ አልተቆጠቡም ፡፡

 

ይህን የፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ  እቅድ ለማገዝ የኢትዮጵያ ፤ የኡጋንዳና የጅቡቲ  መከላከያ ሀይሎች  ድጋፋቸውን አሳይተዋል ሲል  CGTN ዘግቧል፡፡