ካርቱምና ጁባ የጋራ ድንበራቸውን ክፍት ለማድረግ መስማማታቸውን አስታወቁ

ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን በፀጥታ ሁኔታና ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር በነገው እለት ከሚያደረጉት ጎብኝት አስቀድሞ አራት የድንበር ማቋረጫ ቦታዎችን ለመክፈት ተስማምተዋል ።

ካርቱም እኤአ ከ2012 ጀምሮ ጁባን የሱዳንን ተቃዋሚዎች በማስታጠቅ ስትከስ ቆይታለች   ፡፡  

በደቡብ ሱዳን ሁለት አዋሳኝ አካባቢዎች ከ2011 ጀምሮ  ሱዳንን ሲፋለም መቆየቱን ያወሳው የሱዳን ተሪቡን ዘገባ፤አሁን የተደረገው ስምምነት ሀገራቱ ለሚያደርጉት ትብብር ዋና መሠረት መሆኑን አስነብቧል፡፡

በካርቱም መከላከያ ሚኒስቴር በተደረገው ስብሰባ የሱዳን መከላከያ ሚኒስተር አዋድ ኢቢን ኦፍ እና የደቡብ ሱዳን አቻቸው ኮል ማኛን ጁክ ትላንት ባደረጉት ውይይት በመስከረም 2012 የተፈራረሙትን የፀጥታ ውል ብሎም በተባበሩት መንግስታት የተደገፈ የድንበር ቁጥጥር ኃይል ዙርያ መክረዋል፡፡

ሀገራቱ የጋራ ደህንነት ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ እና በጋራ የተቋቋመው  ኮሚቴ ወደ ተግባር እንዲገባ ብሎም በሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት መካከል ያሉትን ችግሮችን ለመፍታት ተስማምተዋል፡፡ በስምምነቱ መሰረትም ፈጥኖ ወደ ተግባር መግባት ይገባል ሲሉ የሱዳን መከላከያ ሚኒስትረ ኢቢን ኦፍ  ተደምጠዋል፡፡

የሁለቱ ሃገራት  ወታደራዊ ስምምነት የግንኙነት መሥመራቸውን በማሻሻል የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነት ወደ ተሻለ ደረጃ የደርሰዋል ሲሊም ኢቢን ኦፍ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ሱዳኑ ጁክም በበኩላቸው የፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ካርቱምን የመጎብኘት ሀሳብ ከፕሬዝዳንት አል-በሽር ጋባዥነት መቅረቡን አንስተዉ ጉብኝቱ  የሁለትዮሽ ግንኙቱን ለማጎልበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ጉብኝቱ የጋራ ግንኙነቶችን ለማበረታታትና በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ያግዛል፤ በተለይም በድንበር አካባቢ ዙርያ የተደረጉትን የትብብር ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳል ሲሉም ጁክ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት መከላከያ ሚኒስትሮች በሚመለከታቸው በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች  ጥሩ መግባባት ላይ ደርሰዋልም ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ መርሃ ግብር መሠረት ፕሬዚዳንት ኦማር አልባሽር እና ሳልቫኪር የደህንነት ስምምነቱን በመጪው ሐሙስ ህዳርን 2 ከሰዓት በኋላ እንደሚፈራረሙ ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡