በሶማሌ ላንድ ምርጫን ተከትሎ በተካሄደ ተቃውሞ ሁለት ሰዎች ተገደሉ

በሶማሌ ላንድ የተካሄደውን ምርጫን ተከትሎ በተካሄደው ተቃውሞ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ ።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የድምጽ አሠጣጡ አግባብ አልነበረም በሚል ምክንያት ባሰሙት ተቃውሞ ሰዎች መሞታቸው እየተነገረ ነው፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ የዋዳኒ ፓርቲ ደጋፊዎች ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል  ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት አህመድ ሞሐመድ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ላለመወዳደር መወሰናቸውን ተከትሎ  በቀጣይ  ሀገሪቱን የሚያስተዳድረውን ሰው ለመምረጥ በሀገሪቱ ምርጫ መካሄዱ  የሚታወስ ነው፡፡    

ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ በምርጫው ከተሳተፉ ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የድምጽ አሠጣጡ አግባብ አልነበረም በሚል ያሰመውን ተቃውሞ ተከትሎ በሶማሊላንድ ሪፐብሊክ  ሁለት ሰዎች ለሞት መዳረጋቸው ነው የተገለጸው፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ የዋዳኒ ፓርቲ ደጋፊዎች  በሀገሪቱ ሶስት ዋና ዋና ከተሞች መንገዶችን በመዝጋት፤ ጎማዎችን በማቃጠል እና የተለያዩ ተሸከርካሪዎች ላይ እና የንግድ ድርጅቶች  ላይ ድንጋይ በመወርወር ምርጫው  ተጭበርብሯል የሚል  ተቃውሞቸውን አሰምተዋል፡፡

በዋና ከተማዋ ሀርጌሳ በተቀሰቀሰ አመጽ አንድ ሰው ሲገደል ሌላኛው ደግሞ በቡራኦ ከተማ በተከሰተ ረብሻ መሞቱ ታውቋል፡፡ በሰሜን ምስራቅ ሳናግ ቀጠና በምትገኘውና በትልቅነቷ በምትጠቀሰው  ኢርጋቮ ከተማ ደግሞ ተቃዋሚዎቹ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል፡፡

ግጭቱን ተከትሎም የሶማሊላንድ የፖሊስ ጄነራል መኮንን አብድላሂ ፋዳል ኢማን ፖለቲከኞች አመጽን ማስነሳት እንደሌለባቸው  አስጠንቅቀው ሁሉም ሰው እንዲረጋጋና ሰላምን እንዲያሰፍን ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡  የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

እንደ ሶማሊ ላንድ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ገለጻ ከሆነ  የድምጽ ቆጠራው እየተካሄደ ሲሆን ውጤቱም በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ይፋ ይደረጋል፡፡

ተቃውሞው የተቀሰቀሰው በምርጫው ለፕሬዚዳንትነት የዋዳኒ ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት አብዱራህማነ ሞሐመድ አብዱላሂ የምርጫውን ግልጸኝንት አስመልክተው ጥያቄ ባቀረቡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነው፡፡

አብዱላሂ በምርጫው ከገዢው ኩልሚዬ ፓርቲ መሪ ሙሴ ቢሂ እና ከጀስቲስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ፓርቴ መሪ ፈይሰል አሊ ወራቤ ጋር ሌላ የፕሬዚዳንትነት ጊዜን ላለማሳለፍ የወሰኑትን የወቅቱን ፕሬዚዳንት ለመተካት ሲፎካከሩ ነበር፡፡

የዋዳኒ ፓርቲ ቃል አቀባይ እንደገለጹት የምርጫ ቦርድ ኮሚሽኑ ፓርቲያቸው የምርጫውን የአሰራር ስህትት አስመልክቶ  ያቀረበውን ቅሬታ ባለማስተናገዱ የፓርቲው አባላት ከድምጽ ቆጠራው እራሳቸውን አግለዋል ። 

ቃል አቀባዩ አያይዘውም ፓርቲያቸው በሶስት የሀገሪቱ ክልሎች ውስጥ የተጭበረበሩ የምርጫ ሳጥኖች ሲዘዋወር መመልከቱን ገልጻዋል፡፡  

ፓርቲያቸው ያቀረበው ክስ ግን በምርጫ ቦርዱ ውድቅ ተደርጓል፡፡ የምርጫ ቦርዱ ሊቀመንበር አብዲቃድር ኢማን ዋርሳሜ ምንም አይነት የምርጫ ሳጥኖች መጭበርበር እና ሌሎች ስህተቶች አልተከሰቱም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የድምጽ አሰጣጡን የተከታተሉትና በእንግሊዝ መንግስት የሚደገፉት 60 አለም አቀፍ ታዛቢዎች የምርጫውን ሂደት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት የምርጫ ህጎች ላይ ጥቃቅን የሆኑ ስተቶችን ከማስተዋላቸው በቀር አጠቃላይ የምርጫው ሂደት አለም አቀፍ የምርጫ ህግጋትን የተከተለ እንደነበር አረጋግጠዋል፡፡

የማህበራዊ ሚዲያዎች መዘጋትና የመራጮች የምርጫ ሂደቱን ያለመረዳት ችግር በምርጫ ሂደቱ የተስተዋሉ ችግሮች እንደነበሩም   አስታውሰዋል፡፡

የምርጫው ዋነኛ ጉዳይ እንደምን ጊዜውም ሶማሌላንድ እንዴት አለማቀፍዊ እውቅናን እና  ተቀባይነትን ማግኘት ትችላለች የሚል ነበር፡፡

 በጣሊያን ቅኝ ግዛት ውስጥ ወድቃ የነበረችው ሶማሊያ ሶማሊላንድ የሉአላዊት ሶማሊያ አካል እንድትሆን ትፈልጋለች፡፡ነገር ግን በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ወድቃ የነበረችውና እ.አ.አ በ 1991 እራሷን ከሶማሊያ ያገለለችው ሶማሌ ላንድ ደግሞ በሁለት እግሯ የቆመች ሉአላዊት ሀገር መሆን ትፈልጋለች፡፡

በምርጫው ለፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩት ሁሉም እጩዎች ሉአላዊት ሀገር የሆነች ሶማሌላንድን ይደግፋሉ ነገር ግን ይህን እውን ለማድረግ ሁሉም የሚከተሉት መንገድ የተለያየ ነው፡፡

የድምጽ ቆጠራውን መጠናቀቅ ተከትሎ ወደ ስልጣን የሚመጣው ፕሬዚዳንት ሀገሪቱን ለሚቀጥሉት 5 አመታት የሚያስተዳድር ይሆናል፡፡ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመኑን ካጠናቀቀ በኃላም ለዳግም ምርጫ የመወዳደር እድል እንደሚኖረውም ኦል አፍሪካን ዶት ኮም ዘግቧል፡፡