የሱዳን ወታደራዊው አገዛዝ ከሲቪል አስተዳደር ጋር ሥልጣን ለመጋራት ተስማማ

የአልበሽርን መውረድ ተከትሎ ሥልጣን የተቆናጠጠው የሱዳን ወታደራዊ አገዛዝ ከተቃዋሚው ጎራ ጋር ሥልጣን ለመጋራት ተስማማ።

ወታደራዊው አገዛዝ እና የሃገሪቱ ተቃዋሚ ኃይል 'ሉዓላዊ ምክር ቤቱን' በፈረቃ ለመምራት መስማማታቸውን  አደራዳሪዎች አብስረዋል።

አደራዳሪው የአፍሪቃ ሕብረት እንዳስታወቀው፣ ወታደራዊው እና ሲቪሉ ኃይል ገለልተኛ አጣሪ ቡድን አቋቁመው በቅርቡ የተከሰቱ ግድያዎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያጣራሉ።

የወታራዊው አገዛዝ ከሲቪሉ ጋር ሥልጣን ለመጋራት የመወሰን ዜና ሱዳንውያንን በደስታ አደባባይ ላይ ወጥተው እንዲፈነድቁ ያስደረገ ሆኗል።

ወታደራዊው አገዛዝ ሥልጣን ይልቀቅ ያሉ ሱዳናውያን ዋና ከተማዋ ካርቱምን አጨናንቀዋት ከርመዋል፤ በሕዝባዊ አመፁ ሳቢያም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት ወታደራዊ አገዛዝና የተቃዋሚው ጎራ እርቅ እንዲያወርዱ ሲጎተጉቱ ከርመዋል።

የአፍሪካ ሕብረቱ አደራዳሪ ሞሐመድ ሐሰን ሌባት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ወታደራዊውና ሲቪሉ አገዛዝ ሉዓላዊ ምክር ቤት አቋቁመው ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በፈረቃ ይመራሉ። ከዚህ ጊዜ መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ በሃገሪቱ ምርጫ ይደረጋል።

ሕዝባዊ አመፅ ከመንበራቸው የፈነገላቸው የሱዳን የቀድሞ ፕሬዝደንት ኦማር ሐሰን አል-ባሽር ከሥልጣን ከወረዱ ወዲህ ሱዳን የከፋ ሕዝባዊ ተቃውሞ አስተናግዳለች። ለዚህ ደግሞ ምክንያት የነበረው አል-ባሽርን የተካው ወታደራዊ አገዛዝ ሥልጣን አሳልፎ ለመሥጠት ፈቃደኛ አለመሆኑ ነበር። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)