የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሕመት በሱዳን ፖለቲካ ኃይሎች መካከል የተፈረመውን የሕገ መንግሥት ረቂቅ መነሻ ስምምነት አደነቁ።
ስምምነቱ ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሲቪል አስተዳደር ለመሔድ የሚያስችላት እና አፍሪካ የራሷን ችግሮች በራሷ ለመፍታት ላላት ፍላጎት ወሳኝ ተግባር ነው ማለታቸውን ህብረቱ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አትቷል።
አያይዞም፣ ሊቀመንበሩ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች፣ ሲቪሎች እና ወታደራዊ አካላት የሀገራቸውን ፍላጎት ከምንም ነገር በላይ በማስቀደም ልዩነቶቻቸውን መፍታት በመቻላቸው እንኳን ደስ አላችሁ ማለታቸውን ገልጿል።
በተጨማሪም ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና አጋሮቻቸው ሱዳን እና የሽግግሩ ባለሥልጣናት ሀገሪቱ የምትገኝበትን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ለመሻገር እንድትችል የበለጠ ጥረት እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን አመልክቷል።
የሱዳን ሕዝብ እና መንግሥት ለሰላም፣ መግባባት እና ብልጽግና ያላቸውን ጥያቄ ለማገዝ የአፍሪካ ኅብረት አሁንም ድረስ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁሟል።
(ምንጭ:- የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን)