በደቡብ ሱዳን አውሮፕላን አደጋ ሞት አልተከሰተም

49 ተጓዦችን አሳፍሮ ከሰሜን ሱዳን ዋኡ ከተማ ወደ ጁባ ሲበር የነበረው የደቡብ ሱዳን አውሮፕላን ተከስክሶ ምንም የሞት አደጋ አለመድረሱ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጄምስ ፒቲያ ሞርጋን ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እደገለጹት 43 የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ አምስት የበረራ አስተናጋጆች፣ ከቻይናና ኤርትራ አንዳንድ ተሳፋሪዎች በበረራው ላይ ነበሩ፡፡

አውሮፕላኑ 500 ኪሎሜትር ከበረረ በኋላ ዋኡ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲሞክር ከእሳት አደጋ ተሽከርካሪ ጋር ተላትሞ ነው አደጋው ያጋጠመው፡፡

አውሮፕላኑ መከስከሱን ተከትሎ በእሳት ከመያያዙ በፊት ሁሉንም ተሳፋሪዎች ማውጣት መቻሉንም ታውቋል፡

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች ወደ ዋኡ ሆስፒታል እንደተወሰዱና ሕክምና ከወሰዱ በኋላ በርካቶቹ ደህና በመሆናቸው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡

አደጋው የደረሰው ትላንት ከሰዓት በኋላ እንደነበር አምባሳደር ሞርጋን አክለው ገልጸዋል፡፡

ደቡብ ሱዳን ጁባ እና ማላካል ተብላው የሚጠሩ ሁለት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማሪፊያዎች እንዳሏት ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡