በሶማሊያ በድርቅ ምክንያት የተከሰተው የሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰ መሆኑ ተመለከተ

በሶማሊያ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ፡፡

በሀገሪቱ ካለፈው ህዳር እስከ የካቲት 2009 ዓም 257 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን አመልክተዋል ፡፡

ከነዚሁም ውስጥ 4 ሺህ 300 ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸውን ነው የገለጸው ፡፡

በፈረንጆቹ ከ2017 መግቢያ አንስቶ በኮሌራ በሽታ ከተያዙ 13 ሺህ ሰዎች ውስጥ ከ300 በላይ በበሽታው መሞታቸውን የድርጅቱ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ አስታውቀዋል፡፡

ዘንድሮ ለሶማሊያ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ ቃል ከተገባው 864 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 31 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ብቻ መገኘቱን ነው የተጠቆሙት ፡፡

በሀገሪቱ ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በረሀብ አደጋ ውስጥ ያሉና አፋጥኝ እርዳታ ካልተገኘም አብዛኞቹ ለሞት አደጋ እንደሚዳረጉም የመንግስታቱ ድርጅት አስጠንቅቋል-(ዥንዋ) ፡፡