ድርጅቱ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት የድርቅ ተጎጂዎች ድጋፍ ማድረግ አለመቻሉን አስታወቀ

የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት በምስራቅ አፍሪካ አገራት ለሚገኙ ይድርቅ ተጎጂዎች ድጋፍ ማድረግ አለመቻሉን አስታወቀ ።  

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው መረጃ በምሰራቅ አፍሪካ ሀገራት ባለፉት አመታት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በርካቶች አሁንም ድረስ ችግር ላይ  መሆናቸውን ጠቅሶ፤ነገር ግን ከተከሰተው ድርቅ አኳያ የሚፈለገውን ድጋፍ ማድረግ አልተቻለም ብሏል፡፡

ስለዚህም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በቀጠናው ያለውን ችግር ለመቅረፍ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሪፖርቱ የአስቸኳይ እርዳታ የሚያሰፈልጋቸው 20 ሚሊየን ሰዎች በቀጠናው እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን፤ በሶማሊያ ብቻ እንኳን 6 ሚሊየን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ያሰፈልጋቸዋል ነው የተባው፡፡

ሀገራቱ ከድርቅ በተጨማሪ በቀጠናው እየተከሰተ ያለው የእርስ በእርሰ ግጭትና አለመረጋጋት ሌላው ችግር እንደሆነና ይህ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ተመልክቷል ፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት በታየው የዝናብ እጥረት ምክንያት የተባባሰው ይህ ድርቅ÷ በሰዎች ብቻ ላይ ሳይሆን በእንሰሳትም ላይ ሞትን ሲያስከትል ቆይቷል፡፡

በሶማሊያ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ህፃናት በተመጣጠነ የምግብ እጥረት አደጋ ላይ መሆናቸውን መረጃው ጨምሮ ያሳያል፡፡

በተለይ ደግሞ  የንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረት የኮሌራ፣ የኩፍኝ እና የተቅማጥ ወረርሽኝ በቀጠናው ለመሰፋፋቱ ዋንኛ ምክንያት ሆኗል ነው የተባለው፡፡ 

በመሆኑም የዓለም ባንክ ለ2 ሚሊየን ሰዎች ለምግብ ፣ ለንፁህ ውሃ እና ለመሠረታዊ የህክምና ቁሳቁሶች የሚሆን 90 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ከዚህም ውሰጥ 60 ሚሊየን ዶላሩ ለሶማሊያ ባፋጣኝ የሚሰጥ ሲሆን÷ የተቀረው 30 ሚሊየን ዶላር  ደግሞ ለደቡብ ሱዳን የሚሰጥ እንደሆነ መረጃው ጠቁሟል፡፡

የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት እንዲሁም የተለያዩ ድርጅቶች በመተባበር በቀጠናው የተጋረጠውን ችግር ለመቅረፍ ርብርብ ላይ መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡