1492ኛው የመውሊድ በዓል በግብፅ በአደባባይ እንዳይከበር ተደርጓል

በኢትዮጵያና በጎረቤት ሀገራት የተከበረው  ይኸው የመውሊድ በዓል በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ እና የሀገሪቱ ሶስተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ጊዛ በዓሉ በአደባባይ እንደ ቀድሞ እንዳይከበር  የሃገሪቱ የሱፊ ጠቅላይ ሸንጎ አስጠንቅቋል፡፡

ሸንጎው በዓሉ በአደባባይ እንዳይከበር ያስጠነቀቀው ባለፈው ህዳር 15 ቀን በሰሜናዊ ግብፅ በሚገኘው ሲናይ አል ራውዳ መስጊድ ላይ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ መሆኑን ኢጅብት ስትሬትስ የተሰኘ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡

ከዚህ ቀደም በሃገሪቱ ጥንታዊ ከተማ ካይሮ ከሳላሕ አል ጃፋሪ መስጊድ ጀምሮ እስከ አል ሑሴን መስጊድ ድረስ የሚከበረው የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል ዘንድሮ በተመሳሳይ እንዳይካሄድ የተከለከለው በጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ግብፃውያን ሙስሊሞች ሃዘን ላይ በመሆናቸው ነው ሲሉ የሱፊ ሸንጎ ቃል አቀባይ አህመድ ካንዲል አስረድተዋል፡፡

አል ራውዳ መስጊድ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ፀሎት ሲደርጉ የነበሩ 305 ምእመን የተገደሉ ሲሆን 128 ሰዎች ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወቃል ፡፡

ስለ ጥቃቱ በግልጽ ሃላፊነት የወሰደ አካል ባይገኝም የአሸባሪው ቡድን አይ ኤስ ሰንደቅ አላማ በጥቃቱ ወቅት መታየቱን ከመገናኛ ብዙሀን የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ክስተቱን ተከትሎ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ የሶስት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ማወጃቸውን እና አሽባሪዎች ይንቀሳቀሱበታል ተብሎ በሚታሰብበት የሲናይ ግዛት አካባቢ የአየር ጥቃት እዲፈጽም የግብጽ አየር ኃይልን ማዘዛቸው ይታወሳል፡፡

የአሏህ መልእክተኛ የሆኑት የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል መውሊድ በሒጅራ አቆጣጠር በ7ኛው ምእተ ዓመት መጀመሪያዎቹ አካባቢ አል ሙዘፈር በተባሉ የዒር ቢል ንጉስ መከበር መጀመሩን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በሂጅራ አቆጣጠር ሶስተኛው ወር በሆነው የረቢአል አወል የተወለዱት ነብዩ ሙሐመድ የልደት በዓል መውሊድ በየዓመቱ  የእምነቱ ተከታዩች ባሉበት በተለያዩ የዓለም ሃገራት ላይ ይከበራል፡፡