በደቡብ ሱዳን 1ነጥብ2 ሚሊዮን ዜጎች ከረሀብ በአንድ ደረጃ መውጣታቸውን ድርጅቱ አስታወቀ

በደቡብ ሱዳን ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከረሀብ በአንድ ደረጃ መውጣታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡

 በረሀብ ልኬት መስፈርት መሰረት በጦርነት ውስጥ ባለችው ደቡብ ሱዳን 1ነጥብ25 ሚሊየን ሰዎች ከከፋ ረሀብ አንድ ደረጃ መውጣታቸው ተመልክቷል ፡፡

ዘንድሮ ከረሀብ የወጡት ደቡብ ሱዳናውያን ቁጥር ከአምናው በሁለት እጥፍ የላቀ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ሆኖም በመጪው የፈረንጆቹ አዲስ አመት 2018 የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ የአገሪቱ ግማሽ ያህል ህዝብ በምግብ እርዳታ ላይ ጥገኛ እንደሆነ ይቀጥላል ሲሉ በተመድ የሰብአዊ እርዳታ ሃላፊ ማርክሎው ኮክ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አራት አመታት በደቡብ ሱዳን ያለውን ጦርነት ሽሽት ስደትን የመረጡ ሁለት ሚሊየን ዜጎች አገራቸውን ጥለው ሲወጡ ሰባት ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ እዛው በአገራቸው ወደ ስደተኛ ጣቢያዎች ገብተዋል፡፡

የሰብአዊ እርዳው ሀላፊ ሎው ኮክ ከወርሃ የካቲት ጀምሮ በአገሪቱ የሚታየው ደረቅ የአየር ሁኔታ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የረሀብ ስጋት ሊታይ እንደሚችል ገልጸው ሊከሰት የሚችለውን ረሀብ ለመቀልበስ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በተመድ የሰላም ማስከበር ሀላፊ ጂንፒሬ ላክሮይ ኤክስ በደቡብ ሱዳን ያለው የጸጥታ ሁኔታ የሚያስተማምን አይደለም በማለት የበጋው ወቅትን ተከትሎ በጎሳዎች መካከል ያለውን ግጭት ለሚያባብሱ አማጺዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር እና በአሁኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ታባን ደንግ ደጋፊዎች መካከል በአገሪቱ ደቡባዊ ዩኒቲ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለማሳያነት አንስተዋል–/ኤ ኤፍ ፒ/ ፡፡