70 በመቶ ኬንያውያን በወባ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ተመለከተ

ከኬንያ ህዝብ ውስጥ 70 በመቶው በወባ በሽታ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ተመለከተ ፡፡

በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ኬንያ እ.አ.አ በ2013 ገዳይ ከሚባሉት በሽታዎች መካከል ወባ ቁጥር አንድ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ሃገሪቱ 47 ሚሊዮን ዜጎች ያሏት ሲሆን ከነዚህም መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት በበሽታው የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

እንደ ናይሮቢ ባሉ ዝቅተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸው ከተማዎች ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ኬንያውያን ሳይቀር በሽታው በስፋት ወደሚገኝባቸው አካባቢዎች ቤተሰብ ለመጠየቅ ወይም በተለያየ ምክንያት ሲጓዙ በቀላሉ በበሽታው ሊጠቁ ይችላሉ ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የሃገሪቱ መንግስት በስፋት ከሚገኝባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ አንዷ ለሆነችው የምዕራብ ፖኮት ነዋሪዎች ከ413 ሺ በላይ አጎበሮችን በነጻ በማከፋፈል ላይ ይገኛል፡፡

ሃገሪቱ ባለፉት ዓመታት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ባደረገችው ጥረት አሁን የወባ በሽታ ገዳይነት ከአንደኛነት ወደ ሶስተኛ ደረጃ ሊደርስ ችሏል፡፡

በሽታውን ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በበሽታው ለሞት የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም ሲሉ የምዕራብ ፖኮት ጤና ጣቢያ ዳይሬክተር ኖርበርት አቡያ ገልፀዋል፡፡

አብዛኞቹ ነዋሪዎች ስለ ወባ መከላከያ አጎበር አጠቃቀም እውቀቱ ስለሌላቸው አጎበሩን በአግባቡ እንደማይጠቀሙ  ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

የአካባቢው አስተዳዳሪ ጆንሎን ያንጋፑ ከሌሎች ወቅቶች በተለየ በዝናባማ ጊዜያት የሚመዘገበው የወባ በሽታ ስርጭት ትንበያ ከፍተኛ በመሆኑ ነዋሪዎቹ የሚሰጣቸውን የወባ መከላከያ አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀሙበትም ጠይቀዋል፡፡

በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች አጎበር ለማግኘት የተመዘገቡ ሲሆን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ግን አዳጋች እንደሚሆን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል ሲል ዘ ስታር ዘግቧል፡፡