በሶማሊያ የተከሰተውን ረሃብ ለመታደግ ለጋሾች የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንዲያድርጉ ጥሪ ቀረበ

የአለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች በሶማሊያ የተከሰተውን ረሃብ ለመታደግ ይቻል ዘንድ ለጋሾች የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እንዲያደረጉ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

በዚህ አመት ብቻ 5 ነጥብ 4 ሚሊዬን ሶማሊያውያውያን የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውም ነው የተጠቆመው፡፡

የዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች የ2 ነጥብ 7 ሚሊዬን ህዝቦቿ ህይወት በረሀብ ሳቢያ አደጋ ላይ እንደሆነ በሚነገርላት ሶማሊያ የተጋረጠባትን  የረሃብ አደጋ መፍተሄ ለማበጀት እርዳታ ሰጪዎች የሚያደርጉትን  የሰብዓዊ እርዳታ መጠን እንዲያሳድጉ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት (ኤንአርሲ) በለንደን በተካሄደው የሶማሊያ የሰብአዊነት ጉባኤ ላይ ባወጣው መግለጫ መሠረት ዛሬም በሀገሪቱ ከግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ሰዎች በረሃብ ላይ ይገኛሉ፡፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባለፈው ዓመት ባደረገው የሰብአዊ እርዳታ በሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት  ለመታደግ ከማስቻሉም ባለፈ አስከፊው ረሀብ ከመከሰቱ በፊት ለመግታት ተችሎ ነበር አሁን ግን የሰብአዊ እርዳታ መጠን መቀነስ  አገሪቷን ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ ሊያስገባት ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን የገለጹት በሶማሊያ የሚገኘው የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት ዳይሬክተር ኒግል ትሪክስ ናቸው፡፡

በሶማሊያ የሰብአዊ እርዳታ  ሁኔታዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ መስራት ያስፈለገው በሀገሪቱ  ውስጥ ለተከሰተው ሰብአዊ ቀውስ ትኩረት በመስጠት በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር 2018  በሀገሪቱ ፖለቲካዊ እና የገንዘብ እመርታን ለማመንጨት እንዲቻል ስለመሆኑም ነው የተመላከተው፡፡ 

በተራድኦ ድርጅቶቹ ገለጻ መሠረት ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ውስጥ  በተከሰተው ረሃብ ሳቢያ  ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ዛሬ ላይ የተባበሩት መንግስታት የአስቸኳይ ጊዜ  የረሃብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ባስቀመጠው ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ፡፡

ድርጅቶቹ በመግለጫቸው እንዳመላከቱት እ.ኤ.አ በ2018 ድርቅ እና የእርስ በርስ  ግጭቶች ተባብረው የደቆሱአትን  ሀገር  መልሶ ለማቋቋም እና ለመገንባት የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢው ማህበረሰብ  1ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያስፈልገዋል፡፡ 

ባለፈው ዓመት ለጋሾች መንግስታዊ ተቋማትና ኤጀንሲዎች የረሀብ  ማስጠንቀቂያውን  ተከትሎ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠታቸው  ሌላ ረሃብ እንዳይከሰት ለመከላከል ስለመቻሉና  በዚህ አመትም ሁኔታው አስቸኳይ መሆኑን በመጠቆም  5ነጥብ4 ሚሊዮን ሶማሊያውያን የሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ነው የተባለው፡፡

በመግለጫው መሰረት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከ 300 ሺ  በላይ የሚሆኑ ሕፃናት በከፍተኛ ደረጃ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጋለጡ ሲሆን 48 ሺ የሚጠጉት ሕፃናት ደግሞ በተመጣጠነ ምግብ እጥረቱ በከፋ ሁኔታ በመጎዳታቸው ሳቢያ የሞት ስጋት ከፊታቸው ተጋርጦባቸዋል፡፡

በቀደሙት አመታት ከሶማሊያ 1 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች  ከቀያቸው መፈናቀላቸው ሲነገር ባለፈው ዓመት ብቻ  1ነጥብ 1 ሚሊየን ሰዎች ደግሞ በሀገሪቱ  በደረሰው ድርቅ እና ግጭት ምክንያት ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሶማሊያ ውስጥ የሚሠሩ ከ30 በላይ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች  በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘውን  ሀገር አበዳሪዎቿ ያለባትን እዳ ቢሰርዙላት ሞቃዲሾ ለ ኢንቨስትመንት ምቹ አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችል የገንዘብ አቅም ስለማግኘቷ ነው የተናገሩት፡፡ 

እንደ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ገለጻ ከሆነ የሶማሊያ የውጭ ዕዳ 5 ቢሊዮን ዶላር ነው፤ነገር ግን ሞቃዲሾ የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከተጀመረበት ከሁለት አስርት ዓመታት ጀምሮ ያለባትን እዳ ለማቃለል ምንም ጥረት ስላላደረገች ተቋሙ ተጨማሪ ብድር ሊሰጣት አይችልም፡፡ 

ይሁንና ከአይ ኤም ኤፍና ከአለም ባንክ ባለስልጣኖች ጋር ለመወያየት በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙት የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን ካይሪድም የተራድኦ ድርጅቶችን ሀሳብ በመጋራት የእዳ ስረዛ እንዲደረግላቸው ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የዘገበው ሽንዋ ነው፡፡