በዴሞክራቲክ ኮንጎ 13 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ለሰብዓዊ እርዳታ ተጋላጭ ሆነዋል

አስራ ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በዲሞክራቲክ ኮንጎ ለሰብዓዊ እርዳታ ተጋላጭ መሆናቸው  ተገለጸ ፡፡  

በዴሞክራቲክ ኮንጎ የተፈጠረውን የፖለቲካዊ ቀውስ ተከትሎ ባጋጠመው የምግብ እጥረትና  የኮሌራ ወረርሽኝ 13 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ ። 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በዴሞክራቲክ ኮንጎ እየተባባሰ የመጣው ግጭት አምና በዚህ ወቅት ያስፈልግ የነበረውን የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት በእጥፍ አሳድጎታል ብሏል፡፡         

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የበታች ሹም ማርክ ሎውኩክ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የውስጥ ችግር 13 ሚሊየን ዜጎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡

አገሪቱን እየናጣት ባለው ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ ወሳኝ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡ ሎውኩክ እንደገለጹት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ የዲሞክራቲክ ኮንጎ ህጻናት ለተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ተራራ የመግፋት ያህል አዳጋች ሆኖባቸዋል ነው  ብለዋል፡፡

2 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚሆኑት ህጻናት ደግሞ በዚሁ የተመጣጣነ ምግብ እጥረት ምክንያት ከጤና መታወክ ያለፈ ለሞት የሚያደርሳቸው አስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሎውኩክ  አመልክተዋል ፡፡  

በዲሞክራተክ ኮንጎ ያለው ፓለቲካዊ ቀውስ ያስከተለው መዘዝ ለኮሌራ የተጋለጡ ዜጎችንም ቁጥር ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡ አሁን በአገሪቱ ባለፉት 15 አመታት ታይቶ የማይታወቅ አይነት የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ በዝምታ እየታለፈ ያለ መጠነ ሰፊ ጾታዊ ጥቃት በተለይም ህጻናትን ኢላማ አድርጎ እየተከናወነ እንደሆነም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ በሥልጣን የመቆየት ህልማቸው እና የተቀዋሚዎች ይህ እንዳይሆን መታገል በዲሞክራቲክ ኮንጎ ደም አፋሳሽ የእርስበርስ ጦርነት ቀስቅሶ አገሪቱንም ዜጎችንም እየጎዳ ይገኛል፡፡

እኤአ በህዳር 2016 መደረግ የነበረበት ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች እየተገፋ አሁን ሊካሄድ ቀን የተቆረጠለት የተያዘው ፈረንጆቹ አመት ማለቂያ ታህሳስ ወር ላይ ነው፡፡ የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ግን ይህም አይግረማችሁ እስከቀጣይ አመት ሚያዚያ ወር ድረስ ማካሄድ ከተቻለም ጥሩ ነው ብሏል በመግለጫው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዲሞክራቲክ ኮንጎ የታየው የፖለቲካ ቀውስ መቋጫ ሊኖረው እንደሚገባ አምኖ የፀጥታው ምክር ቤት በምን መልኩ እልባት ቢያገኝ አዋጭ ይሆናል ሲል እየመከረ ስለመሆኑ የአልጀዚራ የኒዎርክ ዘጋቢ ማይክ ሃና ከተባበሩት መንግስታት የኒዎሩክ ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝቶ ዘግቧል፡፡

ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ህገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ በሆነ መልኩ ሥልጣናቸውን ለማራዘም እያደረጉት ያለው ሙከራ አገሪቱን ዋጋ እያሰከፈለ ስለመሆኑ ተሰምሮበታል ብሏል በዘገባው፡፡

በተለይ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የታጠቁ ሀይሎች ከመንግስት ኃይሎች ጋር እየተጋጩ እንደሆነ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ያሉ የጦር መኮንኖችም ያደረጃጀት ኃይል እንደፍላጎታቸው ከህግ በላይ ሆነው እንዲኖሩ እያደረገ ነው፡፡ እነኚህ እና  ሌሎች ምክንያቶች ተዳምረው  ስደትም ሌላው ለአገሪቱ ዜጎች ፈተና ሆኗል ተብሏል፡፡

የሚያስፈልገውን ያህል እርዳታ ለማቅረብ ከለጋሾች ገንዘብ ማሰባሰብ ብዙ ጊዜ ፈተና የሚሆንበት የመንግስታቱ ድርጅት በተያዘው የፈረንጆች አመት ለዲሞክራቲክ ኮንጎ እርዳታ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ቢሉም እስካሁን አሰባስቦ በእጁ የሚገኘው ገንዘብ ከጠቅላላው አስፈላጊው የገንዘብ መጠን 4 በመቶ ብቻ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል ፡፡