ታንዛኒያ በአገሪቱ የሚገኙ 170 የጤና ተቋማትን አቅም ለማሳድግ እየሠራች ነው

ታንዛኒያ በሀገሪቱ የሚገኙ 170 የጤና ተቋማትን አቅም ለማሳደግ እየሠራች መሆኗን አስታወቀች፡፡

ይህም በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የእናቶች እና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል፡፡

የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ለጤናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡

ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት የሀገሪቱን የነጻነት ቀን ለማክበር ይውል የነበረን ከፍተኛ ገንዘብ በማስቀረት በተለያዩ ሆስፒታሎች የሚስተዋሉ የቁሳቁስ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲውሉ ማድረጋቸውም ለዚህ በማሳያነት ይነሳል፡፡

አሁን ደግሞ በሀገሪቱ የሚገኙ 170 የጤና ተቋማትን አቅም ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ ባለፉት ወራቶች የጤና ኬላዎቿን አቅም ለማሳደግ 161 ነጥብ 9 ቢሊየን ሺሊንግ ወይም 72 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ፈሰስ ማድረጓን ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ ገልጸዋል፡፡

አሁን  የተጀመረው  እንቅስቃሴም 170ዎቹ የጤና ተቋማት  ለወላድ እናቶች  እና  ለህጻናት የሚሰጡትን  የድንገተኛ  ቀዶ  ጥገና  ህክምና  አገልግሎትን  ለማሳደግ   እንደሚያስችል የተጠቆመ ሲሆን፥ በሀገሪቱ  የሚስተዋለውን የእናቶች እና ህጻናት ሞትን ለመቀነስም ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ነው የተነገረው፡፡

በሀገሪቱ ከሚወለዱ 100 ሺህ ህጻናት 556ቱ ለሞት እንደሚዳረጉ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፥ የጤና ተቋማቱን አቅም ለማሳደግ የተጀመረው እንቅስቃሴም  እ.አ.አ በ2020 ይህን ቁጥር ወደ 225 ለመቀነስ እንደሚረዳ ተናግረዋል ፡፡

ፕሬዚዳንቱ 21 ቢሊየን ሺሊንግ ወጪ የተደረገባቸውንና ይህን ጥረት የሚያግዙ 181 ተሽከርካሪዎች ለሀገሪቱ የመድሃኒት ማከማቻ ተቋም አስረክበዋል፡፡

ከግሎባል ፈንድ በእርዳታ መልክ የተገኙት እነዚህ ተሸከርካሪዎች በመላ ሀገሪቱ መድኃኒቶችን እና የህክምና ቁሳቁሶችን የማከፋፈል ተልዕኮ እንደሚኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡

የሀገሪቱ መንግስት ተጨማሪ 268 የጤና ተቋማት መገንባቱን እና በተለያዩ ሆስፒታሎች የስፔሻላይዝድ ህክምናን በማስፋፋት እና በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኝ ዘገባው አመላክቷል፡፡ 

በዚህም በሀገሪቱ የሚገኙ የጤና ተቋማት ቁጥር ወደ 7ሺህ 284 ማደጉ የተገለጸ ሲሆን መንግስትም ተጨማሪ የጤና ተቋማትን በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡(ምንጭ: ዘሲቲዝን)