ዚምባብዌ ከ16 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎችን ከስራ አባረረች

የዚምባብዌ መንግስት ከ16 ሺህ በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያ ነርሶችን ከስራ ማባረሩ ተነግሯል።

የጤና ባለሙያዎቹ ከስራ የተባረሩት በሀገሪቱ የሚስተዋለው የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ደካማ በመሆኑና የስራ አካባቢያቸዉ ምቹ ባለመሆኑ የደሞዝና የጥቅማጥቅም ማሻሻያ እንዲደረግላቸዉ በመጠየቃቸው መሆኑም ነው የተነገረው፡፡

የተሻለ ክፍያና ደመወዝ እንፈልጋለን ያሉ የዚምባብዌ የጤና ባለሙያዎች በሀገር ደረጃ አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግስት ከስራቸዉ አሰናብቷቸዋል።

ነርሶቹ የተሻለ ጥቅምን ፈልገዉ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም በተቃራኒዉ ከመንግስት ያገኙት ምላሽ ግን በርካቶች ያልጠበቁትና አስደንጋጭ ሆኗል።

የጤና ባለሙያዎቹ ጥያቄያቸው ባለመመለሱ ለአምስት ቀናት አድማቸዉን ገፍተዉበታል።

ለ37 አመታት ዚምባብዌን የመሩት ሮበርት ሙጋቤ ባለፈዉ ህዳር ወር ላይ ከስልጣን ከተሰናበቱ በኋላ ወደ ስልጣን የመጡት አዲሱ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን መናንጋግዋ የገጠማቸዉ የመጀመሪያዉ ከፍተኛ ተቃውሞ መሆኑ ነው የተነገረው።

የጤና ባለሙያዎቹ በፖለቲካ አቋማቸዉ ምክኒያት ነዉ አድማ ያደረጉት ያሉት የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ ከ16ሺ በላይ የሚሆኑት በአድማዉ የተሳተፉ የጤና ባለሙያዎች ወዲያዉኑ ከስራቸዉ እንዲሰናበቱ ሲሉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

የቀድሞዉ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ከስልጣን እንዲወርዱ ያደረጉትና የመንግስት ሽግግሩን በተሳካ መልኩ እንዲከናወን ያደረጉት የቀድሞዉ የጦር አለቃ ጀነራል ቺዌንጋ አክለዉም ከስራ በተባረሩት ነርሶች ፋንታ አዲስ የሰለጠኑና ከዚህ ቀደም ከስራ የለቀቁ ባለሙያዎች በተተኪነት ቅጥር ይፈፅማሉ ብለዋል።

የዚምባብዌ ነርሶች ማህበር ረቡዕ ምሽት ባወጣዉ መግለጫ አባላቶቻቸዉ ምንም አይነት የስንብት ደብዳቤ ከጤና አገልግሎቶች ቦርድ እንዳልተሰጣቸዉ ገልፆ ቦርዱ ሀሙስ እስከ 10 ሰዓት ድረስ ማረጋገጫ ካልሰጠ የምክትል ፕሬዝዳንቱን የስንብት ትዕዛዝ እንደማይቀበሉ አስጠንቅቋል።

ማህበሩ አክሎም ፈጣን መልስ ካላገኘን በስተቀር መብታችንን ለማስከበር ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማምራታችን የማይቀር ነዉ ብሏል።

የዚምባብዌ መንግስት በ2010 የተሻለ አፈፃፀም ላላቸዉ ባለሙያዎች ጉርሻ ለመስጠት ቃል ገብቶ የነበረ ሲሆን ዛሬም ድረስ ግን ምንም ክፍያ እንዳልተፈፀመና መንግስት ቃል የተገባዉ 17.1 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ገንዘብ በቅርቡ ለሰራተኞቹ ይከፈላል ቢልም ሰራተኞቹ ግን ያሁኑ አድማ ከዚኛዉ ክፍያ ጋር የሚያገናኘዉ ምንም ነገር የለም በማለት ላይ ይገኛሉ።

ሰራተኞቹ ከዚህ ቀደም አስቸጋሪና ለአደጋ አጋላጭ የስራ ሁኔታ አለ ብለዉ ያቀረቡት ቅሬታ አሁንም ምላሽ አለማግኘቱንና ለጤናቸዉ አደገኛ መሆኑን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት አብዛኞቹ የዚምባብዌ የጤና ባለሙያዎች እጅግ በወረደና ፅዳቱን ባልጠበቀ የስራ ቦታ ላይ እንደሚሰሩና ለስራ የሚያገለግሉ መሰረታዊ የህክምና መሳሪያዎችን እንኳን እንዳላገኙ ይነገራል።

በዚህን ምክኒያት አብዛኞቹ የዚምባብዌ ታካሚዎች የእጅ ጓንት፣ ጥጥና ሌሎች ቁሳቁሶችን ከቤታቸዉ ይዘዉ ለመሄድ እንደሚገደዱ ነዉ የተነገረዉ።
የቀድሞዉ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ይመሰገኑባቸዉ ከነበሩ ጉዳዮች ዋነኛዉ በስልጣን ዘመናቸዉ መጀመሪያ አከባቢ ላይ ነፃ የጤና አገልግሎት ለዜጎች ማቅረባቸዉ እንደነበር ይታወሳል።

ሆኖም ለጤና ዘርፉ የሚደረገዉ ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱ ከ1990ዎቹ ጀምሮ የዚምባብዌ የጤና ዘርፍ ከፍተኛ ዉድቀት እንደገጠመዉ ይታወቃል።

አዲሱ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን መናንጋግዋም የሙጋቤን ተሞክሮ ለማስቀጠል በማሰብ ለእድሜ ባለፀጋዎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ቢሞክሩም አሁንም ግን በዚምባብዌ ያለዉ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ደካማ መሆኑ ተነግሯል።

በዚምባብዌ ዝቅተኛዉ የነርሶች ወርሃዊ ደሞዝ ከ300 ዶላር ያነሰ መሆኑ የተነገረ ሲሆን በአሁኑ አድማም 0.7 ዶላር የነበረዉ የሽፍት የትርፍ ሰዓት ክፍያ በሰዓት ወደ 70 ዶላር እንዲያድግላቸዉና በሰዓት ለስልክ አገልግሎት የሚሰጣቸዉ 150 ዶላር ወደ 750 ዶላር እንዲያድግላቸዉም በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ (ምንጭ፤ አልጀዚራ)