የኢቦላ በሽታ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፑብሊክ ዳግም መከሰቱ ተገለጸ

የቦኢላ በሽታ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፑብሊክ ዳግም መከሰቱ ተገልጿል፡፡

በሰሜን ምዕራብ ኮንጎ ቢያንስ የ17 ሰዎች ሞት ከተሰማ በኋላ የሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎች በኮንጎ የኢቦላ ቫይረስ ዳግም ስለመከሰቱ አረጋግጠዋል።

የመካከለኛዋ አፍሪካ ሀገር ኮንጎ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማክሰኞ እለት እንዳስታወቀዉ 21 ሰዎች ቢኮሮ በተሰኘችዉ ከተማ አቅራቢያ የትኩሳት ስሜት ከተሰማቸዉ በኋላ በተደረገላቸዉ ምርመራ በሁለቱ የኢቦላ ቫይረስ እንደተገነባቸዉ ተነግሯል።

ባለፉት አምስት ሳምንታት ዉስጥ በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል 17 ሰዎች መሞታቸዉ ከወረርሽኙ ጋር ግንኙነት እንዳለዉ ቢነገርም የሞታቸዉ መንስኤ ግን የኢቦላ በሽታ ስለመሆኑ መረጋገጫ አልተገኘም።

ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች መዘጋጀታቸዉን የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር አስታዉቋል።

ምንም አይነት የተረጋገጠ መድሀኒት እንደሌለዉ የሚነገርለት የኢቦላ በሽታ፣ ከ2013 እስከ 2016 በቆየዉ የምዕራብ አፍሪካ ወረርሽኙ ከ11 ሺ 300 በላይ ሰዎችን የገደለ ሲሆን በወቅቱም ጊኒ፣ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ በሽታዉ በስፋት የታየባቸዉ ሀገራት እንደነበሩ ይታወሳል።

በአለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በበሽታዉ ከተያዙ ሰዎች መካከል 50 በመቶዎቹ የመሞት እድላቸዉ ከፍ ያለ ነዉ።

የአለም ጤና ድርጅት በትዊተር ድረገፁ እንዳሰፈረዉ በኮንጎ የኢቦላ በሽታ ስለመከሰቱ መረጃ እንደደረሰዉ ገልፆ ምርመራ ከተደረገላቸዉ አምስት ሰዎች መካለልም በሁለቱ ቫይረሱ ስለመገኘቱ ነዉ የገለጸዉ።

ከአለም ጤና ድርጅት፣ ከቀጠናዉ ሀገራት እና ከአለምአቀፉ ድንበር የለሽ የዶክተሮች ቡድን የተወጣጡ የህክምና ባለሙያዎችም የበሽታዉን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ወደ ስፍራዉ በማቅናት ላይ ስለመሆናቸዉ ተነግሯል።

የአለም የጤና ድርጅትም ለድንገተኛ አደጋ መጠባበቂያ ካስቀመጠዉ ገንዘብ በኮንጎ ለተከሰተዉ የኢቦላ ወረርሽኝ ድጋፍ የሚሆን 1 ሚሊየን ዶላር ስለመለገሱም ነዉ የተነገረዉ።

በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የአለም ጤና ድርጅት ተወካይ የሆኑት ዶክተር አላራንጋር ዮኮዉዴ እንደገለጹት የአለም ጤና ድርጅት፣  አለምአቀፉ ድንበር የለሽ የዶክተሮች ቡድንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የኮንጎን መንግስት ለመደገፍና የተከሰተዉን የኢቦላ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።

አሁን በኮንጎ የተከሰተዉ የኢቦላ ወረርሽኝ  እኤአ በ2017 ግንቦት ወር ላይ በሀገሪቱ ከተከሰተዉ ወረርሽኝ በኋላ፣ አመት ባልሞላዉ ጊዜ ዉስጥ ዳግም የተከሰተ መሆኑ ተነግሯል።

በወቅቱም በበሽታዉ ከተያዙ 8 ሰዎች መካከል የ4ቱ ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነዉ።

የኢቦላ በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለም ላይ የተገኘዉ እኤአ በ 1976 ላይ ሲሆን በደም ንክኪ፣ በሰገራና በሌሎች የሰዉነት ፈሳሾች ምክንያት የሚተላለፍ በሽታ ስለመሆኑም ይነገራል።

ትኩሳት፣ የጡንቻ ህመም፣ የድካም ስሜት፣ ደም የተቀላቀለዉ ተቅማጥና ማስመለስ የበሽታዉ ምልክቶች እንደሆኑም ተነግሯል።

ይህ ገዳይና ፋታ የማይሰጥ የቫይረስ በሽታ ኢቦላ የሚለዉን ስያሜ ያገኘዉ በዛዉ በኮንጎ ከሚገኝ ኢቦላ ከተሰኘ ወንዝ ነዉ ሲል አልጀዚራ በዘገባዉ አስታዉሷል።