በሶማሊያ የተከሰተዉ ድርቅ በሀገሪቱ አስከፊ ረሃብ ሊያስከትል እንደሚችል የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ

በሶማሊያ የተከሰተዉ ድርቅ በሀገሪቱ አስከፊ ረሃብ ሊያስከትል እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።

በመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ የሆኑት ማርክ ሎውኮክ እንዳስታወቁት በሶማሊያ የተከሰተዉ ድርቅ ሀገሪቱን አስከፊ ወደ ተባለ ረሃብ ሊከታት ይችላል።

ቀድሞ ሀገሪቱ በዚህን ወቅት አማካኝ የዝናብ ስርጭት ታገኛለች ተብሎ የተገመተ ቢሆንም በተቃራኒዉ ሀገሪቱ በ35 አመታት ታሪኳ አጋጥሟት በማያዉቅ ድርቅ መመታቷ ነዉ የተነገረዉ።

የመንግስታቱ ድርጅትም ከአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ በጀቱ 45 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያክሉን ለሶማሊያና ለሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ድጋፍ እንዲዉል መመደቡ ተሰምቷል።

ድርጅቱ ከሶማሊያ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሌሎች የቀጠናዉ ሀገራት የምግብ፣ የመጠጥ፣ ዉሃና ሌሎች የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ማቀዱን አስታዉቋል።

ሆኖም በሶማሊያ የተከሰተዉ ድርቅ አስከፊና የሚያስከትለዉ ሰብዓዊ ቀዉስም ከፍተኛ እንደሚሆን በመገመቱ ከአጠቃላይ 45 ሚሊየን ዶላሩ 30 ሚሊየኑ ለሶማሊያ የሚለገስ መሆኑ ይፋ ሆኗል።

አሁን በሶማሊያ የተከሰተዉ ድርቅ 2.2 ሚሊየን የሶማሊያ ዜጎችን ለከፋ ረሃብ ሊዳርጋቸዉ እንደሚችልም ተገምቷል። ይህም በሀገሪቱ በረሃብ የተጠቁ ዜጎች ቁጥርን ባለፈዉ ጥር ወር ላይ ከነበረበት በቀጣዩ መስከረም በ40 በመቶ ከፍ እንዲል ያደርገዋል ተብሏል።

የመንግስታቱ ድርጅት ለቀጠናዉ ሀገራት ከመደበዉ 45 ሚሊየን ዶላር ዉስጥ 10 ሚሊየን ዶላሩ ለኢትዮጵያ፣ ቀሪዉ 5 ሚሊየን ዶላር ደግሞ ለኬንያ የሚሰጥ መሆኑ ተነግሯል።

አሁን በሶማሊያ ያለዉ የድርቅ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ በተያዘዉ የፈረንጆቹ አመት መጨረሻ ላይ ቢያንስ 5.4 ሚሊየን ሶማሊያዊያን የረሃብ ስጋት ዉስጥ ይወድቃሉ። ከዚህ ዉስጥም 2.2 ሚሊየን ዜጎች ለአስከፊ ረሃብ የመጋለጣቸዉ እድል ከፍተኛ ስለመሆኑ ነዉ የተነገረዉ። ይህንን ተከትሎም የመንግስታቱ ድርጅት አሁን ለሀገሪቱ የመደበዉ የአደጋ ጊዜ በጀት በታሪክ ከፍተኛ ከሚባሉት የገንዘብ መጠኖች አንዱ ነዉም ተብሏል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎዉኮክም ሶማሊያዊያን በአስቸጋሪ ተፈጥሮ ሁኔታ ላይ መሆናቸዉን ገልፀዉ÷ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሀገሪቱን ዜጎች ለመታደግ የሚቻለዉን ሁሉ እንዲያደርግ ተማፅነዋል።

በሀገሪቱ የተከሰተዉ ከፍተኛ ድርቅ የዉሃ እጥረት በማስከተሉ በርካቶቹ ሶማያዊያን ከንፅህና ጉድለት በሚከሰቱ በሽታዎች እየተጠቁ መሆናቸዉንም ኃላፊዉ አመላክተዋል።

ሶማሊያ በአሸባሪዉ አልሸባብ የሚደርስባት የሽብር ጥቃትና መከራ አልበቃ ብሎ ለአመታት ያጋጠሟት የድርቅ አደጋዎች በርካታ ዜጎቿን ለሞትና ለእንግልት ዳርገዋል። በፈረንጆቹ 2011 በሀገሪቱ የተከሰተ ረሃብ ብቻ ቢያንስ የ260 ሺህ ዜጎቿን ነፍስ እንደቀማ የመንግስታቱ ድርጅት ያወጣዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

(ምንጭ:-ፕረስ ቲቪ)