በቴክሳስ ህገወጥ ስደተኛ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንዲባረሩ የጠየቀችው መምህርት ከሥራዋ ተሰናበተች

በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት አንዲት የሁለተኛ ደረጃ መምህርት ህገወጥ ስደተኛ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንዲባረሩ የዶራናልድ ትራምፕን እርዳታን በትዊተር ገጿ መጠየቋን ተከትሎ በምላሹ ፎርት ወርዝ የተሰኘው ትምህርት ቤት አባሯታል።

ጆርጂያ ክላርክ የተባለችው ይህችው መምህርት በትዊተር ገጿ ባሰፈረቸው መልዕክት "ትምህርት ቤቱ ከሜክሲኮ በመጡ ህገወጥ ስደተኞች ተሞልቷል። ትምህርት ቤቱ ይህንን የሚያጣራ ሰው ሊመድብ ይገባል፤ ተማሪዎቹም ሊባረሩ ይገባል" ብላለች።

በትዊተር ገጿ ላይ የፃፈችው መልዕክት በይፋ የሚታይ እንዳልመሰላትም ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር ገልጻለች።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችና የመብት ተሟጋቾች ትምህርት ቤቱ ኮንትራቷን እንዲያቋርጥ መጠየቃቸውን ተከትሎ የትምህርት ቤቱ ቦርድ እንድትባረር ወስኗል ነው የተባለው።

በዚህ ሳምንት ማክሰኞ የተባረረችው መምህርት ይግባኝ ለመጠየቅ አስራ አምስት ቀናት እንዳላትም ተገልጿል።

አንድ የስደተኞች መብት ተሟጋች ቡድንም መምህሯ "ትምህርት ቤቶቹን ወደ መጠረዢያ ቦታነት የመቀየር ፍላጎት እንዳላት" ገልፆ ቦርዱ በወሰደው አፋጣኝ እርምጃም ምስጋናውን ችሯል።

"ፎርት ወርዝ ከ86 ሺህ ተማሪዎች በላይ የሚማሩበት ነው፤ ዋናው አላማችንም ማንኛውም ተማሪ መድልዎና መገለል ሳይገጥመው ተከብሮ የሚማርበት ቦታን መፍጠር ነው" በማለትም ትምህርት ቤቱ ስለ ውሳኔው አስታውቋል።

የትምህርት ቤቱን ውሳኔ የተቃወሙትም አልታጡም፤ የፎርት ወርዝ ሪፐብሊካን ሴቶች የተባለ ቡድንም መምህርቷን ደግፎ፤ ውሳኔውን ህገ መንግስቱ የሰጣትን የመናገር ነፃነት የጣሰ ነው ብሏል።

የአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በምንም ሁኔታ ያሉ ስደተኞችን የህዝብ ትምህርት ቤቶች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብለው እንዲያስተምሩ የደነገገ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶችም የስደተኛ ወላጆችን ስለ ህጋዊነታቸው መጠየቅ አይችሉም። ህጋዊ ባይሆኑ እንኳን ሪፖርት ማድርግ አይችሉም። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)