በኬንያ ከኢቦላ ጋር የሚመሳሰሉ ምልክቶች ያለባት ታማሚ ተገኘች

በደቡብ ምዕራብ ኬንያ ከፍተኛ ሙቀት፣ ራስ ምታት፣ የመገጣጠሚያ ችግሮች፣ የጉሮሮ መቁሰል እንዲሁም ማስመለስ ምልክቶች የታዩባት አንዲት ታማሚ ኢቦላ ሊሆን ይችላል በሚል ግምት ምርመራ እየተደረገባት ነው ተብሏል፡፡

ታማሚዋ በመጀመሪያ ወባ ነው በሚል በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል እየታከመች የነበረ ሲሆን፤ ውጤቷ ግን ወባ እንደሌለባት እንዲሁም ሁኔታዋ በመባባሱ ወደ ሌላ ሆስፒታል ተዛውራለች።

ለብቻዋም ተገልላ እንድትታከም እየተደረገች ነው፤ ወደ በኋላም ተቅማጥ የታየባት ሲሆን በአሁኑ ወቅት ጤናዋ እየተሻሻለ እንደሆነ ተገልጿል።

መጀመሪያ የታየችበት የግል ክሊኒክ ኢቦላ ተከስቶበታል ወደ ተባለው ኡጋንዳ ድንበር ጉዞ አድርጋ ነበር በሚል በጥንቃቄ እንድትያዝ የገለፀ ቢሆንም እሷ የሄደችበት የምስራቅ ኡጋንዳ ክፍል ምንም ነገር እንዳልተከሰተ ተገልጿል።

በባለፈው ሳምንት በኡጋንዳ ኢቦላ የተከሰተው በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ሲሆን፣ ይህም ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ በሚያዋስናት ድንበር እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

የደም ናሙናዋ ለኢቦላ ምርመራ ወደ ናይሮቢ እንደተላከም ታውቋል፡፡ (ምንጭ፡-ቢቢሲ)