ድርጅቱ ለሞንጎሊያ የ5ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ 2ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ላሏት ሞንጎሊያ  የ5ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ ።

ድጋፉ የሃገሪቷ የሸቀጥ ዋጋ መቀነስና ተፈላጊነት ማነስ  ያስከተለባትን የምጣኔ ሃብት ግሽበት ለማካካስና የፋናንስ አቅሟን ለማጠናከር የተደረገ ሲሆን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቷን ያበረታዋል ተብሏል፡፡ 

ሞንጎሊያ ሩስያና ቻይና የሚያዋስኗት በዓለም 18 ግዙፍ ሩቅ ምስራቃዊት ሃገር ናት፡፡ አጠቃላይ የህዝብ ብዛቷ 3 ሚልየን ያልሞላ ማለትም 2.8 ሚልየን ብቻ ነው ።

የምጣኔ ሃብት ምንጯ  በማዕድን፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሃገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው  የሸቀጥ ዋጋ መቀነስና ተፈላጊነት ማነስ ምጣኔ ሃብቷን በጂጉ እንደጎዳው የቢቢሲ መረጃ ያሳያል፡፡

 በተለይም የሃገሪቱን ምርት ከሚገዙ ሃገራት መካከል 90 በመቶውን ድርሻ ትወስድ የነበረችው ቻይና ፍላጎቷ በመቀነሱ የሞንጎልያን የምጣኔ ሃብት መቀዛቀዝ ዋነኛ ነው ተብሏል፡፡

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ የሃገሪቱን ግሽበት ለማካካስና የፋናንስ አቅሟን ለማጠናከር 5.5 ቢልየን ዶላር ድጋፍ አድርጎላታል፡፡ ድጋፉም ከኤስያ ልማት ባንክ፣ ከዓለም ባንክ፣ ከጃፓን፣ ከኮሪያና ከቻይና የተገኘ ነው ተብሏል፡፡

አሁን የተደረገላት የገንዘብ ድጋፍ ለአጠቃላይ ህዝቧ ይከፋፈል ቢባል እንኳ ለያንዳንዳቸው በነፍስ ወከፍ ከ1ሺህ 900 ዶላር በላይ ይደርሳቸዋል፡፡

በጥቅሉ አንድ የመሰረተ ልማት ስራ ላይ ይዋል ቢባልም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስገንብቶ ረብጣ ገንዘብ ይተርፈዋል፡፡

ድጋፉ የአገር ውስጥ የገንዘብ ገበያዎች ላይ ያለውን ጫና  እና የታክስ ጭማሬውን ለመቀነስ እንደሚረዳ ድርጅቱ በድረ ገፁ አስነብቧል፡፡

የግብርና እና የቱሪዝም ስራዎቿን እንድታጠናክርም ይረዳታል ተብሏል፡፡ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የሃገሪቱ የምንዛሬ መጠን ዝቅተኛ እንደነበረ ቢቢሲ አውስቷል፡፡ ( ምንጭ: ቢቢሲና የአይ ኤም ኤፍ ድረሰ ገጽ)