ኳታር በሶማሊያ አየር ክልል ያላትን የበራራ ቁጥር አሳደገች

ኳታር ከባህረ-ሰላጤው ሃገራት ማዕቀብ በኋላ  በሶማሊያ የአየር ክልል ያላትን የበረራ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጓን  ተመለከተ ፡፡

ሳዑዲ አረቢያና ሌሎች የአረብ ሃገራት ሽብርተኞችን ትረዳለች በሚል በኳታር ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን መጣላቸው ይታወቃል፡፡

ይህን ተከትሎ ቢያንስ 15 የኳታር አየር መንገድ በረራዎች በሶማሊያ የአየር ክልል መደረጋቸውን አንድ የሶማሊያ ሲቪል አቪየሺን ባለስልጣን ገልጸዋል፡፡

ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአቪዬሺኑ ባለስልጣን አንደገለጹት ኳታር ባለፈው ሰኞ ከባህረ-ሰላጤው ሃገራት ጋር የነበራት ግንኙነት ከመሻከሩ በፊት በየቀኑ አንድ ወይም ሁለት የኳታር አውሮፕላኖች በሶማሊያ የአየር ክልል በረራ ያደርጉ ነበር፡፡

ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብጽ፣ ባህሬን ፣ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ካቁረጡባትና የትራንስፖርት መንገዶቻቸውን ከዘጉባት ወዲህ ኳታር የሶማሊያን የአየር ክልል እንድትጠቀም አስገድዷታል፡፡

የባህረ-ሰላጤው ሀገራት አየር መንገዶች ማለትም ኢሚሬትስ፣ ኢቲሀድ፣ ኢጅፕት ኤይር እና የሳውዲ አረቢያ አየር መንገድን የመሳሰሉት ወደ ካታር ምንም አይነት በረራ እንደማይኖራቸው ካስታወቁ  ሳምንታት አልፈዋል ፡፡

ግዙፉ የካታር አየር መንገድ በበኩሉ ወደነዚህ ሀገራት ለጊዜው በረራውን ማቆሙን ያስታወቀ ሲሆን ወደ ሌሎች ሀገራት ለመብረርም ቢሆን ሀገራቱ የኳታር አየር መንገድ የአየር ክልላቸውን መከልከላቸው ብዙም ትኩረት ወዳልነበራቸው የበረራ አቅጣጫዎች ለመዞር አስገድዶቸዋል፡፡

የኳታር መዲና ዶሃ ዋነኛ የአለም አቀፍ ትራንስፖርት እምብርት መሆኗ ይታወቃል፡፡