የኳታር አየር መንገድ የ2017 ምርጥ የአየር መንገድ በመባል ተመረጠ

የኳታር አየር መንገድ እኤአ በ2017 የዓለም  ምርጥ  አየር መንገድ በመሆን  ተመረጠ ።

አየር መንገዱ በ2016 አሸናፊ የነበረውን የኤምሬትስ አየር መንገድን በመብለጥ ነው ለዚህ ክብር የበቃው፡፡

አጋጣሚው በጎረቤቶቿ መገለል ለደረሰባት ኳታር መጽናኛ ሆኗታል፡፡

በኳታር ላይ የበረራ ማዕቀብ ከጣሉባት ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ንብረት የሆነው የኤምሬትስ አየር መንገድ እኤአ በ2016 የዓለም ምርጡ የአየር መንገድ ተብሎ መመረጡ  ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ለሽብርተኞች ድጋፍ ታደርጋለች በሚል ከጎረበቶችዋ የተለያዩ ማዕቀቦች የተጣሉባት የኳታር አየር መንገድ ግዙፎቹን የሲንጋፖርና ንብረትነቱ የጃፓን የሆነው አና የአየር መንገዶችን በማስከተል ነው በአንደኝነት የተቀመጠው፡፡

የአምናው አሸናፊ ኤምሬትስ ወደ አራተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለ ሲሆን የሆንግ ኮንጉ ካቲ ፓስፊክ፣ የታይዋኑ ኢቫና ሉፍታንዛ አየር መንገዶች ከ5ኛ እስከ 7ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

ኢትሃድ፣ ሃይናን እና ጋሩዳ ኢነዶኔሺያ ደግሞ ክ 8 እስከ 10ኛ ደረጃ ተሰቷቸዋል፡፡

የኳታር አየር መንገድ በአንደኝነት ሲመረጥ ይህ ለ 4ኛ ጊዜው ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በ2011፣ 2012 እና በ2015 ማሸነፉ ይታወቃል፡፡

ግዙፉ የብሪትሽ  አየር መንገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ደረጃው እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡

እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ2006 ዓም አሸናፊ የነበረው የብሪትሽ አየር መንገድ ዘንድሮ በ40ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ አስገራሚ ሆኗል፡፡

 ባለፈው አመት 26ኛ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

ቨርጂን አትላንቲክ፣ኤር ሊንጉስ፣ ኤሮ ፍሎትና የኖርዌይ አየር መንገድ ከብሪትሽ አየር መንገድ በላይ መሆን ችለዋል፡፡

በተጨማሪም አላስካ አየር መንገድ ከ60ኛ ወደ 36ኛ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ76ኛ ወደ 48ኛ እና የሳዑዲ አየር መንገድ ደግሞ ከ82ኛ ወደ 51 ደረጃቸውን በማሳድግ ከፍተኛ መሻሻልን ያሳዩ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡  ( ምንጭ: ቴሌግራፍ)